በአዋሽ ወንዝ ታንኳ ተገልብጣ የጠፉት ስድስት ሰዎች በ24 ሰዓታት ፍለጋ አልተገኙም

1189

አዳማ ሰኔ 10/2010 በአዋሽ ወንዝ ላይ በተገለበጠችው  ታንኳ ምክንያት  የጠፉትን 6 ሰዎች ፍለጋ  ለ24 ሰዓታት የተደረገው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን ፖሊስ ገለፀ ።

የዋናተኞችን ቁጥር በመጨመር ፍለጋው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት ትናንት ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ከተገለበጠችው ታንኳ አዋሽ ወንዝ ውስጥ ገብተው ደብዛቸው የጠፋው ሶስት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ፍለጋ ለ24 ሰዓታት የተደረገው ጥረት እስከ አሁን ውጤት አላስገኘም፡፡

18 ሰዎችን አሳፍራ የአዋሽ ወንዝን በማቋረጥ ላይ የነበረች ታንኳ በደራሽ ውሃ የወንዙ ፍሰት በመጨመሩ ተገልብጣ በአካባቢው ህብረተሰብ ርብርብ የ11 ሰዎች ህይወት ማትረፍ ተችሏል፡፡

በአደጋው ህይወቷ ያለፈው የአንዲት ሴት አስከሬን የተገኘ ሲሆን ስድስት ሰዎች መጥፋታቸውን በትናንትናው ዜና ተገልፆ ነበር ።

ከወንጂና ከዝዋይ የተወጣጡ 8 ዋናተኞችን ጨምሮ ፖሊስ ፣ የአካባቢው ህብረተሰብና የጠፉት ሰዎች ቤተሰቦች ላለፉት 24 ሰዓታት በፍለጋ ላይ ሲሆኑ እስከ አሁን ድረስ የተገኘ ፍንጭ የለም ተብሏል ።

በህይወት የመኖራቸው ጉዳይ የጠበበ ቢሆንም አስከሬናቸውን ለማግኘት  ግን ፍለጋው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ከሰጡት ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

ታንኳዋ እንደተገለበጠች አስከሬኗ ወዲያውኑ የተገኘው እናት አብሯት ወንዙን ሲሻገር የነበረው የ11 ዓመት ልጇ በህይወት ተርፏል፡፡

ወንዙ ውስጥ ገብተው ከጠፉት ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ትናንት መገለፁ ይታወሳል ።