በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 123 ነጥብ 5 ሚሊዮኑ ፀደቀ

1659

ወልዲያ ሰኔ 10/2010 በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው የክረምት ወቅት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 123 ነጥብ 5 ሚሊዮኑ በተደረገለት እንክብካቤና ጥበቃ መፅደቁን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የደን ልማት ባለሙያ አቶ ጋሻው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፈው የክረምት ወቅት 226 ነጥብ 7 ሚሊዮን አገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላው ችግኝ በግልና በወል ይዞታና በተቋማት ዙሪያ ተተክሏል፡፡

ለተተከለው ችግኝ ህብረተሰቡ ባደረገው ጥብቅ ክትትልና እንክብካቤ 123 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆነው መጽደቁ ባለፈው ሚያዚያ ወር በተካሄደ ቆጠራ ተረጋግጧል።

የፀደቀው ችግኝ 23 ሺ ሄክታር መሬት የሸፈነ ሲሆን የዞኑን የደን ሽፋንም ከ11 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደጉንም አስታውቀዋል።

በመጭው ክረምትም የተለያየ ዝርያ ያላቸው 233 ሚሊዮን ችግኝ በ43 ሺ ሄክታር መሬት ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።

እስካሁንም 96 ሚሊዮን የመትከያ ጉድጓድ በአርሶ አደሩ መቆፈሩንም አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

ከተዘጋጁት ችግኝ ውስጥ 25 ነጥብ 2 ሚሊዮን ያህሉ የእንስሳት መኖ ሲሆኑ ቀሪው ዋንዛ፣ ወይራ፣ ጽድ፣ ግራርን ጨምሮ ሌሎች አገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ናቸው።

በዘንድሮው የችግኝ ዝግጅት 152ሺ ያህል አርሶ አደሮችና 265 ማህበራት መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

በጋዞ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር ደምሌ ተስፋው በበኩላቸው ቀደም ሲል ያለሙት 4ሺ የባህር ዛፍ ተክል እንዳላቸው ገልፀው ዘንድሮም 5ሺ ባህር ዛፍ ከሞዴል ችግኝ ጣቢያዎች ገዝተው ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 11 ነዋሪ አርሶ አደር ካሳ ከተማ በበኩላቸው ቀደም ሲል 500 የባህር ዛፍና ከ600 በላይ  የግራር ችግኝ ተክለው ያለሙ ሲሆን በተያዘው ክረምትም ልማቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።