የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ኖቤል ሽልማት ለተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት ወሳኝ ነው- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

83
አዲስ አበባ መስከረም 30 ቀን 2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያገኙት የሰላም ኖቤል ሽልማት አገሪቷ የጀመረችውን ሁለንትናዊ ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል አጋዥ መሆኑን የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸውን ተከትሎ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በአስተያየታቸውም የኖቤል ሽልማቱ በአገሪቷ የተጀመሩትን ሁለንተናዊ ለውጦች ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጵጥሮስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሽልማት ላከናወኑት ተግባር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። ሽልማቱ በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያም ይሁን የተረጋጋች አገርን በመፍጠር ረገድ እየተሰሩ ያሉትን ጅማሮዎች የሚያስቀጥል ይሆናል ብለዋል። የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ ሉአላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብረሃም ደስታ በበኩላቸው፣ ሽልማቱ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ጊዜያዊ አለመረጋጋት ወጥታ ወደ አገራዊ አንድነት እንድትጓዝ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል። በአገሪቷ እየተካሄደ ባለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጦች ላይ የተሻለ እንቅሰቃሴ እንዲኖር የማድረግ እድል ይፈጥራልም ነው ያሉት። የመላው ኢትዮጵያን ብሄራዊ ንቅናቄ ፕሬዝዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራው በሰጡት ሃሳብም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሽልማት በተለይ ትላንት የአንድነት ፓርክን ባማስመረቁበት ማግስት መሆኑ ድሉን ድርብ ያደርገዋል ብለዋል። ከአገር አልፎ ለጉረቤት አገራት ትልቅ ማስተማሪያ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በአሁኑ ሰዓት በአገሪቷ ውስጥ የተለያዩ የውስጥ ችግሮች ቢኖሩም የተሰሩ ብዙ መልካም ጅማሮዎች በመኖራቸው በውጭ የተሻለ ስም የተጎናጸፍንበት ነው ብለዋል። የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሮበሌ ታደሰም ሽልማቱ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በአገሪቷ ሲከናወኑ የነበሩ ትላልቅ ተግባራት ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ አሁን እያጋጠሟት ያሉትን ፈተናዎች ለመሻገርና  የጀመረችውን ሁለንትናዊ ለውጥ ወደ ፊት ለማስቀጠል የሚያበረታታ ሽልማት ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። የፓርቲ አመራሮቹ በዓለም አደባባይ እንዲህ ያሉ ድሎችን መጎናጸፍ የመልካም ጅማሮዎች ማሳያ በመሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም