የተቋራጮች የአቅም ውስንነት በፕሮጀክቶች ላይ መጓተት ፈጥሯል

81
ባህርዳረ ኢዜአ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም .... የተቋራጮች የአቅም ውስንነት መኖር በመስኖና መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ላይ  ከታቀደላቸው ጊዜ ከጥፍ በላይ እንዲዘገዩ እደረገ ነው -የአማራ ክልል ውሃ ፣መስኖና ኢነርጅ ቢሮ በአማራ ክልል የተቋራጮች የመገንባት አቅም ውስንነት ለህብረተሰቡ የንጹህ መጥጥ ውሃና የመስኖ ውሃ ፕሮጀክቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት ፈጥሮብኛል ሲል የክልሉ ውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ። ለፕሮጀክቶች መጓተት የአቅም ውሱንነት ብቻ ሳይሆን  ለግንባታዎቹ ያለቀለት ዲዛይን አለመቅረብ ችግር ነው ሲሉ ተቋራጮች ተናግረዋል። በጉዳዩ ዙሪያ አማካሪዎችና ተቋራጮች የተሳተፉበት ውይይት ትናንት ማምሻውን በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል። የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መለስ ስንታየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክቶችንና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እያሰፈሰሰ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም 400 ከፍተኛና መካከለኛ የመጠጥ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች በተቋራጮች አቅም ውስንነት በተየዘለዛቸው የጊዜ ገደብም ሆነ ጥራታቸውን ጠብቀው በመጠናቀቅ ረገድ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ተናግረዋል። የፕሮጀክቶቹ መዘግየትም በተጠቃሚነት ከሚያሳድረው ተፅእኖ ባለፈ ከፍተኛ የሆነ ተጨማሪ በጀት በመጠየቅ የክልሉን የገንዘብ አቅምም እየተገዳደረ ይገኛል። በመጓተቱም አዳዲስ ተቋማትን መገንባትና ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን መድረስ እየተቻለ በውስን ቦታዎች ብቻ ረጅም ጊዜና በርካታ በጀት አላግባብ እየፈሰሰ መሆኑን ተናግረዋል ። በዚህም ንጹህ መጠጥ ውኃም ሆነ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተቀመጠውን ክልል አቀፍ ግብ ለማዳረስ እንቅፋት መፍጠሩን ገልፀዋል ። ባለፉት ዓመታት የመስኖ አውታሮችን ለመዘርጋት ሰፊ ጥረት ቢደረግም በክልሉ በመስኖ ለመልማት ካለው አቅም በአሁኑ ወቅት ከ10 በመቶ በታች መሆኑን ጠቅሰው የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከ80 በመቶ በላይ እንደሆነ አስቀምጠዋል። የግንባታዎቹ መዘግየት በፈጠረው ተጽእኖም በዚህ ዓመት ነባር ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ችግር ማጋጠሙን አቶ መለሰ አስረድተዋል። በክልሉ በዘርፍ የተሰማሩ ተቋራጮች ቁጥራቸው ከ100 እንደማይበልጥ አመልክተው ከተቋራጮች አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። የዚህ ውይይት አላማም  ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያቶችን መለየትና ተቋራጮች ከመንግስት የሚፈልጉትን ድጋፍ በመለየት በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት በሚፈታበት መንገድ ተወያይቶ ለመተግበር እንደሆነም ጠቁመዋል። "የሃይሉ አበጀ ህንፃና ውሃ ነክ ስራዎች" ጠቅላላ ስራዎች ባለቤት ኢንጂነር ሃይሉ አበጀ እንደ ሚሉት ለፕሮጀክቶች መጓተት የተቋራጩን የአቅም ውስንነት ብቻ ሳይሆን የቢሮው የዲዛይን ችግርና ለፕሮጀክቶች ግንባታ የሚሰጠው ጊዜ አጭር በመሆኑ ነው። ፕሮጀክቶች ዲዛይን የሚደረጉት በቢሮው አማካሪ መህንዲሶች  አማካኝነት በመሆኑ  ተቋራጮች ወደ ስራ ሲገቡ ዲዛይኖች በተፈለገው ልክ ተጠናቀው አይቀርቡም ብለዋል። ስለሆነም የተቋራጮች የአቅም ውስንነት የለም ባይባልም የቢሮው የጊዜ ገደብ አሰጣጥና የዲዛይን ችግር ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አብራርተዋል። የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጀት  መጠጥ ውሃና ፍሳሽ ዘርፍ  ሃላፊ ኢንጂነር ሀይሌ ጌታቸው በበኩላቸው  ፕሮጀክቶች ጨረታ የሚወጣባቸው  ዲዛይኑ ከተጠናቀቀ ከሁለት አመትና ከዚያ በላይ ነው። ይሄ ደግሞ በአካባቢው የሚኖረውን ነባራዊ ሁኔታ  በተለይ የህዝቡ አሰፋፈር ስለሚቀያየር  የዲዛይን ለውጥ ለማድረግ እያሰገደደ መምጣቱን ገልፀዋል። በተለይ የመጠጥ ውሃ ፐሮጀክቶች ላይ  የውሃው መገኛ ጉድጓድ ሳይጠና የውሃ ማከፋፈያዎች ዲዛይን ተደርገው ከተሰሩ በኋላ የውሃው መገኛ ዲዛይን ሲደረግ በቀላሉ ሊገኝ ባለመቻሉ ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቃል። በመሆኑም ችግሩን የአንድ ወገን ብቻ ማድረግ አይቻልም ያሉት ኢንጂነር  ሀይሌ በተለይ ቢሮው ፕሮጀክቶችን ዲዛይን ሲያደርግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማዘጋጀት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። ተቋራጮች የአቅም ውስንነተ እንዳለባቸው ቢታመንም አቅም አንጻራዊ በመሆኑ ቢሮው እንደ መንግስት በሱ በኩል የሚከወኑ ተግባራትን በጥራት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በውይይቱ ላይ ተቋረቀጮች፣ አማካሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም