ሜክሲኮ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለመደገፍ የመተባበር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

87
መስከረም 30 /2012 ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገቷን ለማፋጠን በምታከናውናቸው ስራዎች ላይ ሜክሲኮ ለመደገፍና በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች። የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ የሜክሲኮ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁሊያን ቬንቱራን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የውይይታቸው ትኩረት የነበረውም በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች መሆኑ ተገልጿል። የሜክሲኮ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁሊያን ቬንቱራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ኢትዮጰያ የምጣኔ ሀብት ዕድገቷን ለማፋጠን እያከናወነች ያለችውን ስራ ሜክሲኮ ታደንቃለች። አገራቸው ይህንኑ ለመደገፍ በተለያዩ ዘርፎች የአቅም ግንባታና ቴክኒካዊ ስራዎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ፤ ኢትዮጵያና ሜክሲኮ 70 ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል። የአገሮቹን የንግድና ኢንቨሰትመንት ትስስር በማጠናከር በኩል ግን ብዙ ስራዎች አለመሰራታቸውን ገልጸዋል። የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማጠናከር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አስረድተዋል። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁሊያን ዶክተር አብይ የ2019 የሠላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታና የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል። ሁለቱ አገሮች ግንኙነት የጀመሩበትን 70ኛ ዓመት በማስመልከት በአዲስ አበባ ኤግዝቢሽን ማዕከል የፎቶ አውደ ርእይ እንደሚከፈት ታውቋል። በሜክሲኮ ደግሞ ለዚሁ መታሰቢ የሚሆን ልዩ የቶምቦላ ሎተሪ መዘጋጀቱ ተገልጿል። ኢትዮጵያና ሜክሲኮ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1949 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም