በትግራይ የቱሪዝም ልማት ዘርፉ መነቃቃት እያሳየ ነው

725

መቀሌ ኢዜአ መስከረም 30 /2012….. በትግራይ የቱሪዝም ልማት ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ ።
በክልሉ ዘርፉን ለማሳደግ በተከናወኑ የተለያዩ የማስተዋወቅ ስራዎች የቱሪስት ፍሰትና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እየጨመረ እንዲመጣ አድርጎታል ተብሏል ።

በቢሮው የብቃት ማረጋገጥ ሬጉላቶሪ ዳይሬክተሬት ዳይሬክተር አቶ የማነ ገድሉ እንዳሉት ዘርፉ የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጥ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በዓመት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ የተለያዩ የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች ቁጥር ከ21 ሺህ አይበልጡም ነበር ብለዋል።

ዘርፉን ለማበረታታት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ሆቴሎች በመገንባታቸውና የቱሪስት ማረፊያ ሎጆች በመስፋፋታቸው የቱሪስቶቹ ቁጥር ወደ 90 ሺህ ከፍ ብሏል ።

የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በክልሉ መጠናከራቸው፣የጉዞ ወኪሎች  በክልሉ ከተሞች መከፈትም ለዘርፉ እድገት አጋዠ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች አሁን ላይ ከአንድ እስከ አራት ኮኮብ ደረጃ የተሰጣቸው 20 ያህል ሆቴሎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠትመጀመራቸው ለዘርፉ ማደግና ለቱሪስቶቹ ቁጥር መጨመር እገዛ ማድረጉን አቶ የማነ ገልፀዋል ።

ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ በመምጣቱም በዘርፉ ብቻ ከ16 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል ተጠቃሚዎች ማድረግ ተችሏል ።

ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግምበውጭ ሃገራት የሚገኙ የክልሉ ተወላጅ ምሁራንና በክልሉ የሚገኙ አራት ዩኒቨርስቲዎች በቅንጅት ያዘጋጁት የቱሪዝም ልማት ሰነድ በተመረጡ አራት አካባቢዎች በሙከራ ደረጃ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉም ገልጸዋል።

በቢሮው የገበያ ማስተዋወቅ ኬዝ ቲም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዮናስ ታደለ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የዌብ ሳይት ፣ፌስቡክና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ዜዴዎች በመጠቀም የክልሉን እምቅ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ የተከናወነው ስራ እጅግ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ በቱሪስቶች ፍሰት እና በስራ ፈጠራ እድል በየዓመቱ በአማካይ 30 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተያዘው እቅድ ከሞላ ጎደልተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ዮናስ ያመለከቱት።

ያለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በአብነት በማጣቀስም በ2009 በጀት ዓመት ላይ ክልሉን የጎበኙት የተለያዩ ሃገራት ዜጎች 56 ሺህ 469 እንደነበሩና በ2011 በጀት አመት የቱሪስቶቹ ቁጥር ወደ 91 ሺህ 764 ከፍ ማለቱን አመልክተዋል።

የቱሪስት ፍሰቱ የሃገር ውስጥ ጎብኝዎች ሲታከሉበት እጅግ እየጨመረ መጥቷል ያሉት አቶ ዮናስ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም በዛ ልክ እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።

በ2011 በጀት ዓመት ክልሉን ከጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች 115 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን የገለጹት ከፍተኛ ባለሙያው ገቢው የሃገር ውስጥ ጎብኝዎችን እንዳማያካትት ገልጸዋል።

ክልሉን በብዛት ከጎበኙ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች መካከል ጀርመናያዊያን ፣ ኢንግሊዛዊያንና የአሜሪካ ዜጎች እንደሚገኙባቸውም ነው ከፍተኛ ባለሙያው የተናገሩት  ።

በክልሉ ህዝብ ዘንድ ዘርፉን ለማሳደግ የተፈጠረው አዎንታዊ አመለካከትና በክልሉ ውስጥ ያለውን ተነጻጻሪ ሰላም ለዘርፉ እድገት ምቹ መደላድን መፍጠሩንም ከአቶ ዮናስ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።