የኢጋድ አገራት መሪዎች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር በአርአያነት መቀጠሏን አወደሱ

489

መስከረም 30/2012 ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ትብብር እንዲፈጠር እያከናወነች ያለውን ተግባር የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች የጋራ ልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አገራት መሪዎች አወደሱ።

መሪዎቹ በታላቁ ቤተ መንግስት የተከፈተው አንድነት ፓርክ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ስብጥር የሚያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል።

መሪዎቹ ይህን ያሉት አንድነት ፓርክ ለህዝብ ክፍትመሆኑን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ነው።

ፓርኩን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበይ አህመድ ጋር በመሆን የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩቬሪ ሙሶቬኒ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫኪር መርቀው ከፍተዋል።

የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ኬኒያ የሚገጥሟቸውን ማንኛውንም ችግሮች በውይይት እየፈቱ እዚህ ደርሰዋል።

ይህም ጠንካራና ዘመን ተሻጋሪ የሁለትዮሸ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ አገራቱ የቀጠናውን ችግር ለመፍታት በጋራ እንዲሰለፉ አድርጓል ነው ያሉት።

ቤተ መንግስቱን ለማነኛውም ዜጋ ክፍት መሆኑ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር  ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ግልጽ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ አገር ለመፍጠር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያልም ብለዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በቀደመው ጊዜያት እድገትና ለውጥ ሲባል ወደ ሩቅ ምስራቅ አገራት ማየት የተለመደ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ  ግን የእድገትና ሪፎርም መንገድ ምን መምሰል እንዳለበት ኢትዮጵያ ጥሩ ትምህርት እየሰጠች ትገኛለች ብለዋል።

በሱዳን ለተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት የኢትዮጵያ ሚና የላቀ መሆኑን በመጥቀስ መስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሁለቱ አገሮች የቆየ ወዳጅነት አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቂት ቀናት በፊት የሱዳንና ኢትዮጵያ የጋራ ንግድ ምክር ቤት አዲስ አበባ መካሄዱም ትብብሩ እየተጠናከረ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድነት ፓርክን “ታሪካዊ፣ የኢኮኖሚ እድገት ባህልን ሳይበረዝ ተሰናስሎ የሚሄድ መሆኑን ያሳየ ሲሉ ገልጸውታል።

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩሪ ሚሶቬኒም አፍሪካውያን ታሪካቸውን በሚገባ ጠብቀው የማሸጋጋር ክፍተት እንዳለባቸው አስታውሰዋል።

የአንድነት ፓርክ የታሪክ ቅብብሎሽን አስተሳስሮ ከመያዙም በላይ በኢትዮጵያ የቱሪዝም እድገት ላይ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

“በአስከፊ ችግር በወደቅንበት ጊዜ ሳይቀር ኢትዮጵያ ሁሌም ከጎናችን ናት” ያሉት ደግሞ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኬር ማያርዲት ናቸው።

ኢትዮጵያ ከጎናችን ባትቆም ኖሮ ደቡብ ሱዳን የተበባለች ነጻ አገርን እውን የማድረጉ ስራ ሂደት አስቸጋሪ ይሆን እንደነበርም አውስተዋል።

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት በመሪዎች ይሁንታ ብቻ የሚከወን ሳይሆን የቀደመና በህዝብ ለህዝብ የተሳሳረ መሆኑንም አንስተዋል።

ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያዊያን ሁሌም በሯ ክፍት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ  በርካታ ተመሳሳይ ነገር ያላቸው የሶማሊያና የኢትዮጰያ ህዝብችን ወደ ተሻለ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማሻጋጋር እንደሚገባ አንስተዋል።

የአንድነት ፓርክ መገንባት አገራቱ በኢኮኖሚ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ለመተሳሳር የሚያደርጉትን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ፓርኩ የኢኮኖሚ ስብጥር እንዲኖር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም በመጠቆም።