የምክር ቤት አባላት የህዝቡ አንድነት እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

423

አርባምንጭ ኢዜአ መስከረም 29/2012፣ የህዝቡ አንድነትና አብሮነት እንዲቀጥል የምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጋሞ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የዞኑ ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በተጀመረበት ወቅት አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ልሳነወርቅ ካሣዬ እንደገለጹት አባላቱ ተጠሪነታቸው ለወከላቸው ህዝብ ሁለንተናዊ ለውጥ መረጋገጥ መስራት ቀዳሚው ተግባራቸው ነው።

የህዝቡ ዘላቂ ልማት እንዲሁም እኩል ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ሰላም ሲጠበቅ በመሆኑ በጋሞ አባቶችና ወጣቶች የተጀመረው መልካም ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ሀገራዊ ለውጡ  ለህዝቡ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም ውዥንብር በመፍጠር የህብረተሰቡን ሰላምና ልማት የሚጉዱ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት አባላት ለዘመናት የነበረውን የህዝቡ አንድነትና አብሮነት እንዲቀጥል የአመራር ጥበብ በመጠቀም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አፈ ጉባኤዋ ጥሪ አቅርበዋል።

ጉባኤው በአርባምንጭ ከተማ  ለሁለት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ ባለፈው የበጀት ዓመት የዞኑ ዕቅድ ክንውንና በተያዘው የስራ ዘመን ረቂቅ ዕቅድ ዙሪያ በመወያየት ለዘመኑ ስራ ማስፈጸሚያ በጀትና ልዩ ልዩ ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡