ካፍ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ቅጣት አስተላለፈ

67
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 29/2012 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የአምስት ሺህ ዶላር ቅጣት አስተላለፈ። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና ጥሎ ማለፍ ውድድሮች መጠናቀቅ ከነበረባበቸው ጊዜ ዘግይተው መጠናቀቃቸው ይታወሳል። በስፖርት ሜዳዎች ላይ የነበሩ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችና በአገሪቱ የነበሩ አለመረጋጋቶች የፈጠሩት የጸጥታ ችግር ውድድሮቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ነበሩ። ይህን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ክለቦችን የሚያሳውቅበት ጊዜ እንዲራዘምለት ጠይቆ የነበረ ሲሆን የካፍ የውድድር ክፍልም ጥያቄውን ተቀብሎት ነበር። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር አመቱ በተጠናቀቀበት ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በዓመቱ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የወከሉ ክለቦችን ለካፍ አሳውቋል። ይሁንና በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሆኑት መቀሌ ሰብአ እንደርታና ፋሲል ከነማ ክለቦች ከክለብ ላይሰንሲንግ (ፈቃድ) ጋር ያሉ ጉዳዮች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በትክክል ለውድድር ክፍሉ ባለመድረሱ ካፍ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የአምስት ሺህ ዶላር ቅጣት  አስተላልፏል። ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን በመቃወም አስፈላጊ መረጃዎችን በጊዜው የላከ መሆኑን ቢገልጽም ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ካፍ ውሳኔውን ማጽናቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም