ምክር ቤቱ ወደ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚገመት የብድር ስምምነት በዝርዝር እንዲታይ ለሚመለከተው መርቷል

488

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 29/2012 ምክር ቤቱ ከተለያዩ አካላት ጋር ለሚፈጸም የ978 ሚሊየን ዶላር እና 85 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነት ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው የቋሚ ኮሚቴ መራ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው የ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው አካል መርቷል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው ውይይት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ መንግስትና በፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ መካከል ስለሚደረገው የብድር ስምምነት አንዱ ነው።

ብድሩ ለልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ይውላል የተባለ ሲሆን ለዚሁ የታሰበውን 85 ሚሊየን ዩሮ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግስት ከኮሪያ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ መካከል ለብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለውን የብድር ስምምነትም ለዝርዝር እይታ መርቷል።

በተጨማሪም ከዚሁ ባንክ ጋር የከርሰ ምድር ውኃ መስኖ ልማትና የገጠር ግብርና ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ94 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነትም በዝርዝር እንዲታይ ተብሏል።

ለገቢዎች፣ በጀትና ፈይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ የተመራው 170 ሚሊዮን ዶላር የተገመተው ይኸው ብድር ጠቀሜታው የጎላ ነውም ተብሏል።

ከዚህ ባለፈ መንግስት ከዲላ-ቡሌ-ሀሮ ዋጩ የመንግድ ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 64 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነትም ለዝርዝር እይታ ተመርቷል።

የዚህ ፕሮጀክት የብድር ምንጮችም የአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማትና የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት(ኦፔክ) ፈንድ ለዓለም አቀፍ ልማት መሆናቸውም ታውቋል።

በሌላ በኩል ለቆላ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል 350 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነትም ለተመሳሳይ ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ ተመርቷል።

የብድሩ የፋይናንስ ምንጭም የአለም ዓቀፍ ልማት ማህበር መሆኑ የተመለከተ ሲሆን በስድስት ክልሎች የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ይረዳልም ተብሏል።

በተጨማሪም ከዚሁ የዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር የተገኘ 30 ሚሊየን ዶላር ብድር ስምምነትም በዝርዝር እንዲታይ ተብሏል።

ብድሩ ለሁለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን የአንድ ቋት አካውንት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል መሆኑም ተጠቅሷል።

ምክር ቤቱ በተመሳሳይ የመድን ስራ አዋጅን ለመሻሻል የቀረበን ረቂቅ አዋጅና የአነስተኛ ፋይናንስ ስራ አዋጅን ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም በሰዎች የመነገድንና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የተዘጋጀውን አዋጅንም በዝርዝር እንዲታይ ወስኗል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር ላይ የድጋፍ ሞሽን አዳምጧል።