መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ትኩረት መስጠቱ የሚደገፍ ነው...የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

59
አክሱም (ኢዜአ) መስከረም 28 ቀን 2012 መንግስት በተያዘው ዓመት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ያስቀመጠውን አቅጣጫ እንደሚደግፉት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመንግስት የ2012 የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮችና ለፌደሬሽን ምክር ቤቶች ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል። በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚ ምሁር ዶክተር አብርሃ ገብሩ እንዳሉት መንግስት በዓመቱ የዋጋ ንረትን ለመቆጠጣር በትኩረት እንደሚሰራ ፕሬዚዳንቷ ያነሱት ሀሳብ ተገቢና ተቀባይነት ያለው ነው። በአገሪቱ ለዋጋ ንረት መከሰት ዋነኛ ምክንያት የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣምና ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ መሆኑንም አመልክተዋል። ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገቡ ዕድገቶችን ተከትሎ የህብረተሰቡ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዶክተር አብርሃ ፣ በእዚያ ልክ ምርታማነት አለማደግ ለዋጋ ንረት የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል። "በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲስተዋል የነበረው የሰላም መደፍረስ አምራቹ ኃይል ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውንና ምርታማነት እንዳይጨምር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል" ብለዋል። በየጊዜው መልካቸው እየተቀያየረ የሚከሰቱ የሰላም ጉዳዮች በአገሪቱ የዋጋ ንረት እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድርጋቸውንም ጠቁመዋል። መንግስት በተያዘው ዓመት የተረጋጋ ፖለቲካና ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት እንደሚሰራ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተገቢ ስለሆነ እንደሚደግፉት ነው ዶክተር አብርሃ የገለጹት። እንደ እርሳቸው ገለጻ በተያዘው ወር የተመዘገበውን ከፍ ያለ የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር መንግስት በተመረጡ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ጣልቃ ገብቶ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት አለበት። የዋጋ ግሽበቱን በዘላቂነት ለመቆጣጠር ሰላምና መረጋጋትን አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን ገልጸው "ለአቅርቦትና ፍላጎት መጣጣም ምርታማነትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሳደግ ያስፈልጋል" ብለዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለሁሉቱ ምክርቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን ለማድረግ በመንግስት አቅጣጫ መያዙን የገለጹት ተገቢ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ሀጎስ ብርሀነ ናቸው። መንግስት ለገባው ቃል ቁርጠኛ ሆኖ ለምርጫ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች እና ግብአቶች ከወዲሁ ሟሟላት እንዳለበትም መክረዋል። "ምርጫው በተባለው ልክ በአግባቡ እንዲከናወን በተለይ መንግስት ለሰላምና መረጋጋት ስራው ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል" ብለዋል። መምህር ሀጎስ እንዳሉት በቀጣይ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ መንግስት የያዘውን የትኩረት አቅጣጫ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በበርካታ ጉዳዮች  ላይ ያስቀመጡት የመንግስት አቅጣጫ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም ለመተግበር ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ምሁራኑ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም