አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት የአማራ ክልልን ሰላምና ፀጥታ ለማወክ የጀመሩትን ዘመቻ እንዲያቆሙ ተጠየቀ

70
መስከረም 27/2012 አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የአማራ ክልልን ሰላምና ጸጥታ ለማወክ የጀመሩትን ዘመቻ በአፋጣኝ እንዲያቆሙ የክልሉ አመራሮች ጠየቁ። የብሮድካስት ባለስልጣን ችግሩን ለመፍታት ለመገናኛ ብዙሃኑ ሙያዊ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጿል። የአገሪቷ የለውጥ ሂደት ከታገለባቸው ጉዳዮች መካከል የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አንዱ ነው። በዚህም በአሸባሪነት ጭምር ተፈርጀው የነበሩና በአገር ውስጥ እንዳይሰሩ የተከለከሉ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጭምር በነፃነት እንዲሰሩ ፍቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ  ገልጸዋል። ይሁንና ነጻነታቸውንና ሃላፊነታቸውን ባላጣጣመ መልኩ የአማራ ክልልን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርሱና ከእውነት የራቁ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ነው ያሉት። የብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ የብሮድካስት አዋጁን በሚጻረር መልኩ መረጃ የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መኖራቸውን አምኗል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ መገናኛ ብዙሃን የተሰጣቸውን ነጻነት በሃላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙ እንደሚገባ ለኢዜአ ተናግረዋል። የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀውን ስነ-ምግባር ጠብቀው ሚዛናዊ በሆነና የሁሉንም ወገን አስተሳሰብና ፍላጎት ባማከለ መልኩ  እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል። በአሁን ጊዜ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች በጋዜጠኞች ላይ በሚያሳድሩት ጫና ምክንያት ባለሙያዎቹ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ እንደሚቸገሩም ያነሳሉ። ባለስልጣኑ ሙያዊ ትንተናዎችን መሰረት ያደረገ ምክረ ሀሳቦችን የመስጠት ብሎም በብሮድካስት አዋጁ መሰረት የማይሰሩ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ እርምጃ የመውሰድ ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም