በአዋሽ ወንዝ ታንኳ ተገልብጣ የአንድ ሰው ህይወት ሲጠፋ ስድስት ሰዎች የደረሰቡት ጠፋ

1345

አዳማ ሰኔ 9/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን ወንጂ ክልል ዛሬ 18 ሰዎችን አሳፍራ የአዋሽ ወንዝን ስታቋርጥ የነበረች ታንኳ ተገልብጣ ስድስት ሰዎች የደረሱበት መጥፋቱንና የአንዲት ሴት አስከሬን መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በአዋሽ ወንዝ ሁለት ጫፎች በተተከሉ እንጨቶች ላይ ሽቦ በማሰር እየተጎተተች ሰዎችን ወንዝ ስታሻግር  የነበረች  ኋላ ቀር ታንኳ ደራሽ ውሃ  መጥቶ የወንዙ ፍሰት በመጨመሩ ምክንያት አንደኛው  ሽቦ ተበጥሶ ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ የመገልበጥ አደጋ ደርሶባታል።

የዞኑ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት 18 ሰዎችን አሳፍራ ከወንጂ ክልል ወደ ቦኩ ኩሪቡ ቀበሌ ለማሻገር ስትሞክር ታንኳዋ በመገልበጧ ምክንያት የአንዲት ሴት አስከሬን ወዲያውኑ ተገኝቷል።

11 ሰዎች በአካባቢው ህብረተሰብ ርብርብ ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል።

ሌሎች ስድስት ሰዎች  ግን የአካባቢው ዋናተኞች ፣ ፖሊስና ህብረተሰቡ የማያቋርጥ ፍለጋ ቢያካሄድም እስከ አሁን የደረሱበት ማወቅ አልተቻለም።

አስከሬኗ የተገኘው ሴት አብሯት የነበረ የ11 ዓመት ልጇ በህይወት መትረፉንና የደረሱበት ከጠፉት 6 ሰዎች መካከል አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ኮማንደሩ አስታውቀዋል።

ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ፍለጋው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ገልጸዋል።