የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ አገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል

63
መስከረም 27 / 2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የዓለም ባንክ አስታወቀ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዓለም ባንክ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንትን ሰርጂዮ ፒሜንታን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በዚሁ ወቅትም የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ አገር-በቀል የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ማሻሻያ ሪፎርም የተረጋጋ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንደሚያግዝ ሚስተር ሰርጂዮ ፒሜንታ ገልጸዋል። በማሻሻያ እርምጃው የፋይናንስ ተቋማትን አሰራር የማዘመን እና የማስተካከል እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑንም አመልክተዋል። በመንግስት ይዞታ የሚተዳደሩ ግዙፍ የልማት ተቋማትን ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት መደረጋቸው እንደሚያደንቁም ተናግረዋል። መንግስት የጀመረውን አገር-በቀል የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ማሻሻያ ውጤታማነት በቀጣይ ኮርፖሬሽኑ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በግሉ ዘርፍ የገበያ ዕድል ትስስር ዙሪያ ለኢትዮጵያ የጀመረውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ጠቁሟል። የተጀመረው አገር-በቀል የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ማሻሻያ መሰረት በቢዝነስ እና በኢንቨስትመንት ድባብ ዙሪያ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ገልጸዋል፡፡ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ የገበያ ትስስር ውጤታማነት የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማድነቅ፤ በቀጣይ ለሃገር-በቀል የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ማሻሻያ ሪፎርም ውጤታማነት የተቋሙ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም