የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ተካሄደ

428

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 26/2012 የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ተካሂዷል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመንግስትን የ2012 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።

በመንግስት ዋና ዋና አንኳር ጉዳዮች ተብለው ከተለዩት ውስጥ ሠላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ እንደሆነ ፕሬዚዳንቷ አመልክተዋል።

በዚህ ዓመት የሚከናወነው አገራዊ ምርጫ በተቻለ መጠን ባለፉት ምርጫዎች ያጋጠሙንን ግድፈቶች በሚያርም መልክ እንዲከናወን፣ ነጻና ዲሞክራያዊ ሆኖ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆንና የፖለቲካ ልሂቃንንና የምልዐተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፍርድ ቤት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግና ባለፉት ዓመታት እንዲሻሻሉ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ሕጎችን ማሻሻል ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረግ የመንግስት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ሁለት ዓይነት የውኃ አቅርቦት ማለትም የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የመስኖ ውሃ አቅርቦት ለማሳካት መታቀዱን አመልክተዋል።

”በአገራችን ከአገልግሎት ዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ ለማሳደግና በቴክኖሎጂ እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዓመቱ ለኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2012 ዓ.ም. አዲሱን የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊነት እንደሚጀመር ተናግረው፤ ”የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዋና ዓላማዎቹ ትምህርትን በሁሉም መስክ ማዳረስ እንዲሁም የትምህርትን ጥራትና ብቃት መጨመር ናቸው” ብለዋል።

የጤና ዘርፉም የወረዳ ትራንስፎርሜሽንን ማሳለጥ፣ ሆስፒታሎች አገልግሎታቸውን ለጤና ባለሞያዎችና ለሕሙማን በሚመጥኑ መንገድ ማደራጀት፣ ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል ያለው የጤና አገልግሎትና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምንና የሴቶች የልማት ቡድንን አሠራር ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

በ2011 የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግና ብሎም የጾታ እኩልነት ማረጋገጥ ረጅም ጉዞ ላይ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል እንደሚሰራም አመልክተዋል።

”የባሕልና የቱሪዝም ሀብቶቻችንን ለሕዝቦቻችን አንድነትና ሠላም፣ ለሀገራችንም ኢኮኖሚ በሚገባ መጠቀም አለብን” ብለዋል።

የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት በዘርፉ ያገኘነውን መልካም ውጤት የማሳደግ፣ በመግባባትና ትብብር መርሕ ላይ መመሥረት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም፣ ለጎረቤት አገሮች ቅድሚያ የሚሰጥ ፖሊሲን መከተል፣ የውጭ ግንኙነቱ ብሔራዊ ክብርንና የዜጎችን ክብር የሚያስጠብቅ እንዲሆን በማድረግ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

”በምናያቸውና በምንሰማቸው አስደሳች ነገሮች እንደምንደሰተው ሁሉ በዚህ አገር የሚሆነውን ክፉ ተግባር መጠየፍ፤ ተመልሶም እንዳይደገም አስተዋጽዎ ማበርከት የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የግድ ልንሳተፍበት የሚገባ የአገር ግንባታ ጉዞ መሆን ይኖርበታል፡፡”ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የሁሉም ራስ ምታት መሆን እንዳለበት በመግለጽ ለአገር ሰላምና ብልጽግና ሁሉም እንዲባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የተከበሩ አፈ ጉባዔ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

ያለፈው ዓመት በሀገራችን የጀመርነው የለውጥ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ጥረት ያደረግንበት ወቅት ነበር። በፖለቲካ፣ በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ ሥርዓት እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነበረብንን ሀገራዊ ጉድለት ማስተካከል የጀመርንበት ነው። ይሁንና ጉድለቱን በተሟላ ያቃናንበት ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም። አንዳንዶቹም በባሕሪያቸው መዋቅራዊ በመሆናቸው ከአንድ ዓመት አለፍ የሚል ምክንያታዊ ጊዜን የሚጠይቁም ናቸው።

2012 ዓ.ም. የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል። እንደሚታወቀው የለውጡ ጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት በመተግበር ላይ የሚገኘውን የመደመርን ዕሳቤ መሠረት አድርጎ የሚጓዝ ነው። ይህ ዕሳቤ ደግሞ በሦስት ዋነኛ ሀገራዊ ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ ነው። እነርሱም፡ – በሀገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ – ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና – የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም ማሳካት ናቸው። የእነዚህ ዓላማዎች ዋነኛው ማጠንጠኛ ሦስቱን ግቦች ለማሳካት መቻል ነው። እነዚህም፡ – የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ – የሕዝቧን ክብር ከፍ ማድረግና – ብልጽግናን ማምጣት ናቸው።

ኢትዮጵያ ዛሬ አልተጀመረችም፤ የሺ ዓመታት ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ ያከማቸናቸውና ለዛሬና ለነገ ሊጠቅሙን የሚችሉ መነሻ ሀብቶች አሉን። ካከማቸናቸው ሃብቶችና ፀጋዎች መካከል ነጻነትን አስከብረን መኖራችን፣ የረዥም ዘመናት የታሪክና የቅርስ ሀብቶችን ማከማቸታችን፣ እርስ በርስ የተቆራኘ ኅብረ ብሔራዊነትን መፍጠራችን፣ በውጭ ግንኙኘት መስክ ያዳበርነውን ተሰሚነት፣ በአፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ዘንድ ያለን የነጻነት አጋርነት ታሪካችን፣ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የገነባናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ያስመዘገብነው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እያዳበርነው የመጣነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ወዘተ. መጥቀስ ይቻላል። እነዚህን ሀብቶቻችንን አካብተን ለዛሬና ለነገ ብልጽግናችን በመጠቀም የጀመርነውን ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

ያለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎቻችን መልካም ጸጋዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስህተቶችም አሉት። እኩልነትን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን፣ አካታችነትን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ የፍትሕ ሥርዓት መዛነፍን በተመለከተ የተፈጸሙ ስህተቶች አሉ። በቅርቡ ታሪካችን እንኳን ልዩነቶቻችን ላይ የሠራነውን ያህል አንድነታችን ላይ አልሠራንም፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በሚገባው ልክ አላረጋገጠም፣ በሰብአዊ መብት አያያዛችንና በፖለቲካዊ መብቶቻችን ላይ ሰፊ ጉድለቶች ተመዝግበዋል። እነዚህ የተወዘፉ ዕዳዎቻችን ናቸው። ውዝፍ ስህተቶቻችንን ያለ ምሕረት ማረም ይኖርብናል።

እነዚህ መልካም ሥራዎቻችንን ይዘን፣ ያጋጠሙንንም ውዝፍ ዕዳዎች አርመን የምንጓዘው የመጭውን ትውልድ ፍላጎትና መጪውን ሁኔታ ብሩህ ለማድረግ፣ ኢትዮጵያ በርግጥም የህዝቦቿ በተለይም የወጣቶቿ ሀገር ለማድረግ ሲባል ነው። ሀገር በትውልዶች ቅብብሎሽ የምትገነባ በመሆኗ፣ እኛ በትናንቶቹ መሠረት ላይ እንደቆምነው ሁሉ እኛም ለቀጣዩ ትውልድ ከእኛ የተሻለ ሥራ ሠርተን ማስረከብ አለብን። ነገ ከዛሬ የተሻለ መሆን አለበትና።

በያዝነው ዓመት የምናከናውናቸው ተግባራት ሁሉ በእነዚህ ዓላማዎችና ግቦች ላይ የሚያጠነጥኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ግቦቹን ለማሳካት ያላቸውን ድርሻ መገምገም ይኖርብናል። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ ቅኝቶቻቸው ዓላማዎቻቸው እና የሀገር ክብር፣ ግቦቻቸውም የመደመር ግቦች መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

ከላይ በተጠቀሱት ዕሴቶች፣ ዓላማዎችና ግቦች መሠረት የ2012 ዓ.ም. ዋና ዋና የመንግሥት ተግባራት በሚከተሉት አንኳር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ይሆናል።

ሠላምና መረጋጋትን ማረጋገጥን በተመለከተ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ሀገራችንን ወጥረው ከያዟት ችግሮች አንዱ የውስጣዊ መረጋጋት እጦትና በየቦታው የሚከሠቱ የተለያየ ይዘት ያላቸው ግጭቶች መፈጠር ነው። ግጭቶቹን ተከትሎ የመጣው የውስጥ መፈናቀልም በታሪካችን ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ምዕራፍ ሆኗል። በተመሳሳይ ዓመት አገራችን ከጎረቤት አገራት የተሰደዱትን ማስተናገዷን የቀጠለችውን ያህል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በገዛ ሀገራቸው ተፈናቃይ የሆኑበትን አሳዛኝ የታሪክ ገጽ አልፈናል። ይሁን እንጂ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባለፈው አንድ ዓመት በጋራ ባደረጉት ርብርብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የነበረው የውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከመቶ ሺ የማይዘል ሆኗል። እርሱንም ፈትተን ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ወደ ታሪክነት ለመቀየር እየተሠራ ነው፡፡

በመልሶ ማስፈርና ዘላቂ ማቋቋም መርሐ ግብር ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ወደ ተሟላ መደበኛና የተረጋጋ ኑሮ የመመለስ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። መሰል ክሥተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ መፍትሔ አምጪ ሥራዎች ይከናወናሉ። የደኅንነት ተቋማት ችግሮች ከመከሠታቸው በፊት ቀድመው የማነፍነፍ ዐቅማቸው እንዲያድግና ችግር ሲከሠትም በአጭር ጊዜ የማስቆም ብቃታቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራት ይሠራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ፌደራል ፖሊስ ብቁ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ጥናት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ይሸጋገራል። በሂደቱም የአሠራርና የሕግ ማዕቀፎቹን በማሻሻል በአጭር ጊዜ በጠንካራ ዶክትሪን የሚመራ ጠንካራ የፌደራል ፖሊስ ይኖረናል። የክልል ፖሊሶችም አቅማቸውን እንዲያጠናከሩ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ። እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊታችን በሞያ ዐቅም የላቀ እንዲሆን እየተሠሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በአጠቃላይ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን የሕጋዊ ማዕቀፎችና አቅሞችን በማዳበርና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ አሁን በሀገራችን ያለውን አንጻራዊ ሠላም ወደ አስተማማኝ ሠላም ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል፡፡ በቀጣይ ሀገራችን የምታስተናግዳቸውን ሀገራዊ ምርጫ እና ሌሎች ክስተቶች ሠላማዊ በሆነ መልኩ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ይፈጠራል።

ከሠላም ግንባታ አኳያ ዋናው አቅጣጫ ኅብረተሰቡንና የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ዕሴቶች ማዕከል ያደረጉ የዘላቂ ሠላም ግንባታ ተግባራትን መሠረት የሚያደርግ ነው። በርካታ የውይይት መድረኮች በቀጣይነትና በቋሚነት በኅብረተሰብ ደረጃ ለሚካሄዱ የሠላም ምክክሮች ከተለያዩ የኅብረተሰብ አደረጃጀቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አመቻቾችን የማሠልጠን በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ የሀገራችንን ሠላም በማስጠበቅ ረገድ ዋናው ባለቤት ሕዝብ በመሆኑ ያለ ሕዝቡ ተሳትፎ ሠላምን ማስከበርም ሆነ በቀጣይነት ዘላቂ ሠላምን መገንባት የማይታሰብ ነው። በመሆኑም ሕዝቡ ሠላምን በዘላቂነት በመገንባትም ሆነ ሕግን በማክበርና በማስከበር፣ የሠላም መደፍረስ ምልክቶችን ጥቆማ በማድረስና ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት የሠላም ባለቤትነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።

ሠላም በእያንዳንዳችን እጅና ልቦና ውስጥ የሚገኝ ውድ ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም ሌት ተቀን እንዳይናችን ብሌን ልንንከባከበው የሚገባ አንዳችን ለአንዳችን የሠላም ምንጭ እንጂ የስቃይ ምንጭ እንዳንሆን ከቆረጥንና ለተግባራዊነቱ ከተጋን ሠላም በደጃችን፤ በእጃችን ያለ ሀብት ሆኖ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በእርጋታው፣ በአርቆ አስተዋይነቱና ስንዴውን ከእንክርዳዱ በመለየት ብቃቱ ነው፡፡ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ይመዝናል፤ ከዕለት አልፎ ዘላቂውን አርቆ ያስባል፤ የሚሰማውንና የሚያየውን እየመዘነ ምርቱን ከገለባ ይለያል፡፡ ይህንን ታላቅ ሕዝብ እዚህም እዚያም የሚወረወሩ አሉባልታዎች ሊፈትኑት አይገባም፡፡ ስሜት አርቆ አሳቢነትን፣ ግብታዊነትም እርጋታን ሲተኩ ዝም ብሎ ማየት የለበትም፡፡ የሐሰት መረጃዎችን ሳይመዝኑ መነሣትና ግብታዊ እርምጃዎችን መውሰድ የዚህ ታላቅ ሕዝብ መገለጫዎች እንዳይሆኑ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ ምትክ የለሽ አንዲት ሀገራችንን በጋራ ጥረት ሰላማዊ ለማድረግ በአርቆ አስተዋይነት ነገሮችን ሁሉ መጠየቅ፣ መመዘን የሚገባ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መልእክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ።

ይህን ክፍተት ከመሙላት አንጻር መንግሥትም የሕግ የበላይነትን ከማክበርና ከማስከበር ጎን ለጎን የመረጃ ተደራሽነት እንዲሰፋ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፤ ሞያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ለሚሠሩ ጋዜጠኞችም ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል። በቀጣይነትም ባለፈው በጀት ዓመት የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር ኅብረተሰብ ተኮር የሠላም ግንባታ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብሎም ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትም ይከናወናሉ። ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብ ልማት ፕሮግራሞችም የሚካሄዱ ይሆናል።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

የፖለቲካ ሥርዓቱንና ዴሞክራሲን በተመለከተ ፖለቲካዊ መብቶችንና ተሳትፎን አስመልክቶ የምንከተለው መንገድ በመግባባት ፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ ያተኮረና የሀገርን አንድነት በሚያጠናክሩ ዕሴቶች የተቃኘ ይሆናል። መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በሕግ፣ በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በሥርዓት ቀረጻ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል። የጠላትነትና የቡድን ፍረጃ አካሄዶች ቀርተው የመግባባት ፖለቲካ እንዲሰፍን፣ የመነጠልና የመለያየት አካሄዶች ታርመው የትብብርና የአንድነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት ጎልቶ እንዲወጣ ያበረታታል።

በዚህ ዓመት የምናከናውነው ሀገራዊ ምርጫ ሦስት ዕሴቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሠራል። የምናካሂደው ምርጫ በተቻለ መጠን ባለፉት ምርጫዎች ያጋጠሙንን ግድፈቶች በሚያርም መልክ እንዲከናወን፣ ነጻና ዲሞክራያዊ ሆኖ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆንና የፖለቲካ ልሂቃንንና የምልዐተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ይደረጋል።

እነዚህን ሦስት አስፈላጊ ጉዳዮች ለማሳካት የመንግሥት ቁርጠኝነትና ዝግጅት ብቻውን በቂ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ልሂቃኑ እና የሲቪክ ድርጅቶች ቀናነት፣ ተሳትፎና ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ መሥራት ወሳኝ ነው። የዚህን ዓመት ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ከቻልን ቀጣዮቹ የፖለቲካ ሂደቶቻችን በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲመሠረቱ ለማድረግ ዕድል እናገኛለን።

መንግሥት ምርጫው ያለፉ ግድፈቶችን በሚያርም መልክ እንዲከናወን፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ፤ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን እንዲሁም የፖለቲካ ልሂቃንንና የምልዓተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ከመሥራት ባሻገር ሂደቱን ለማሰናከልና ለማጠልሸት የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ተግባራትን በሕግና በሥርዓት የሚያስተካክል ይሆናል። ከሀገራዊ ምርጫው ባሻገር የሚከናወኑ የሕዝበ ውሳኔ ሂደቶችም ከላይ ምርጫውን በተመለከተ በተቀመጡት ሦስቱ ዕሴቶች መሠረት የሚከናወኑ ይሆናሉ። ሕግና ሥርዓት የማስከበሩ ተግባርም በዚያው መልኩ ይካሄዳል።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

የፍትሕ ሥርዓቱን በተመለከተ የዚህ ዓመት ትኩረታችን የፍርድ ቤት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግና ባለፉት ዓመታት እንዲሻሻሉ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ሕጎችን በማሻሻል ላይ ያተኮረ ይሆናል።

የፍርድ ቤት ማሻሻያዎችን ለማከናወን የሦስት ዓመታት መርሐ ግብር ተቀርጾ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን ይህ ዓመት የተጀመረውን አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል። በዚህም መሠረት በሦስት ዘርፎች የሚከናወን የፌዴራል ፍርድ ቤቶችና የዳኝነት ማሻሻያ ዕቅድ ተቀርጾአል። ይህ ማሻሻያ የዳኝነት ነጻነትን፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ማጠናከር፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ማስፋትና የሕግ ዕውቀት እንዲዳብር ማድረግ፣ እንዲሁም የዳኝነትን ውጤታማነትና ቅልጥፍና ማሻሻል የመርሐ ግብሩ ዋና ዋና ትኩረቶች ናቸው።

የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በሚሠራው ማሻሻያ የዳኝነት አስተዳደር ዓዋጅ ማሻሻያ በማከናወን የፌደራል ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን የማስተዳደር አቅም ማጎልበት፤ የፌደራል ዳኞችን የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ደንብ ማጽደቅ፣ በደንቡ ላይ ሥልጠና መስጠትና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ለዳኞች አመቺ የሥራ ሁኔታ እንዲመቻች አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ፤ ዳኞች ሞያዊ እና ተጨማሪ ክህሎቶች የሚያገኙበትን ተከታታይ ስልታዊ ሥልጠናዎችን ማካሄድ፤ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የመገናኛና ግንዛቤ የመፍጠሪያ መድረኮችን ማዘጋጀት፤ እንዲሁም የዳኞችን ነጻነት እና ተጠያቂነት ያገናዘበ የዳኞች ምዘና ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግን ያካትታል፡፡

ውጤታማ እና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር በተያዘው ዕቅድ ደግሞ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አደረጃጀትና ሥልጣን የሚወስኑ ዓዋጆችን ማሻሻያ የማጠናቀቅ፤ የየአዋጁን ማሻሻያ ተከትሎ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደርን የተሻለ ለማድረግ አስፈላጊ አደረጃጀትን የመዘርጋትና ደንቦቹን ማውጣት ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ሕዝቡ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚያቀርበውን ከፍተኛ የአገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ የሚያሥችል፤ በዓመት እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ (250,000) መዛግብት ለማስተናገድ የሚያስችል አወቃቀር መፍጠር፤ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መምሪያ፣ የቁጥጥርና ክትትል ክፍሎችን በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋም እና ማደራጀት፤ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር፤ የዳኝነት አገልግሎት ሥራ ደጋፊ የሆኑትን የአስተዳዳር አካላት ውጤታማነት ማረጋገጥ ዋነኞቹ ትኩረቶቹ ናቸው።

የሕግ ዕውቀት እንዲዳብር ለማድረግ የማኅበረሰብ የሕግ ዕውቀት ማሳደጊያ ፕሮግራም ይከናወናል። ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን የሕግ ዕውቀት በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ሌሎችንም የማኅበረሰብ የሕግ ዕውቀት ማሳደጊያ መስኮችን ያካትታል። የዳኝነት ውጤታማነትንና ቅልጥፍናን ለማሻሻልም የመረጃና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ዐቅምን ለማሳደግ ታቅዷል።

ሕጎችን ለማሻሻል በተያዘው ዕቅድ መሠረት አዲስ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግን፣ አዲስ የንግድ ሕግን እና አዲስ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግን አጸድቆ ሥራ ላይ ማዋል የዚህ ዓመት ዋና ዋና ተግባራት ናቸው። ከሦስቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ከወጡ 60 ዓመታት ያለፋቸው ሕግጋት ናቸው።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

ኢኮኖሚውን በተመለከተ ይህ ዓመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት በተጠናከረ ደረጃ የሚከናወኑበት ይሆናል። ለዚህ ዋናው መሪ ሐሳብ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረግ ነው። የዚህ ዋና ዓላማዎች ሦስት ሲሆኑ እነርሱም – የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት መጠበቅ፣ – የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግና – ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ናቸው።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እነዚህን ዓላማዎቹን ለማሳካት የሚያተኩርባቸው ሦስት ጉዳዮች አሉት። የመጀመሪያው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማስተካከል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን ማሻሻል ነው። የኢኮኖሚ መዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን፣ የኃይል አቅርቦትን፣ የቴሌኮም ዘርፍን ማሻሻልን እና የሎጅስቲክስ ሥርዓትን ማቀላጠፍን ያካትታል። ሦስተኛው የማሻሻያ ፕሮግራሙ ትኩረት ደግሞ የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ ነው። እርሱም የግብርና ምርታማነትን፣ የአምራች ዘርፉን እና የቱሪዝም ዘርፍን ለማሻሻል እንዲሁም የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሪ ሀብት ለማስፋት፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለማቀላጠፍ ትኩረት ይሰጣል።

ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ጋር አብሮ የሚሄደው የንግድ አሠራር የማሳለጫ መንገዱን (Doing Business) ማቀላጠፍ ሲሆን ሀገራችንን ለቢዝነስ እንቅስቃሴ ተመራጭ ሥፍራ እንድትሆን ያለመ ነው። በየተቋማቱ በሕግና በአሠራር ያሉ እንቅፋቶችን ማስተካከል፣ አካሄዱን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የሰው ኃይሉን ብቃት መጨመርና በተለያዩ ተቋማት የተበታተኑ አሠራሮችን ለቅልጥፍና በሚያመች መልኩ ማሰባሰብ በዋናነት ትኩረት የሚደረግባቸው ናቸው።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የተጀመረው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና የማፈላለግ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ ወጣቶቻችን ለሥራ ዲሲፕሊን የሚበቃቸውን ሥልጠና ወስደው፣ ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው እንዲሠማሩም ያደርጋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚውን ከማቃናት አንጻር የተጀመሩ የተጠናከረ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ፣ ከተለያዩ ምንጮች ለልማታችን የሚያግዝ የውጭ ምንዛሪ የማሰባሰብ ተግባር ፣ የውጭ ብድር ጫናን ለማቃለል የዕዳ ማሸጋሸግ ድርድር ሥራዎችና የኤክስፖርት ገቢያችንን በ2012 የማጠናከር ጥረት የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በያዝነው የበጀት ዓመት የተመረጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይንም በሙሉ ወደግል የማዘዋወሩ እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (PPP) የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን የመተግበሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የቴሌኮም ሴክተር እንዲሁም በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኙ የተወሰኑ ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት በከፊል ወይንም በሙሉ ወደ ግል የሚዛወሩ ይሆናል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ የሕገወጥ ንግድን መልክ የማስያዝ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተጠባቂ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመፈጸም እቅም በማሳደግ ኮንትሮባንድ፣ ታክስ ማጭበርበርንና ታክስ መሰወርን፣ እንዲሁም በሕቡዕ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት በማምጣት ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ጤንነት የማሸጋገር የተቀናጀ ሥራ ይከናወናል፡፡

የዋጋ ንረት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህበረተሰብ ክፍሎች በተለይ የሚጎዳ በመሆኑ የዋጋ ንረቱን የመቆጣጠር ሥራ በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራ ይሆናል፡፡ የዋጋ ንረቱ በዋናነት የሚስተዋለው በምግብ ሸቀጦች ላይ ስለሆነ መንግስት የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ በማስገባት የዋጋ ንረቱ ሸማቾችን እንዳይጎዳ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት ሌላው የሚተኮርበት ጉዳይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚያሻሽል ሥራ የመሥራት ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፖሊሲያችንንና አፈጻጸማችንን እንደገና በመፈተሽ ውጤታማ የሆነ የማትጊያ ሥርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህን በማድረግ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ዘርፎች ያለው ምርታማነት የሚያሳድግ ሥራ በትኩረት ይከናወናል፡፡

በአጠቃላይ 2012 በኢኮኖሚው ዘርፍ ፣ ምርታማነትን በማሳደግ ፍላጎት ተኮር የነበረውን ኢኮኖሚያችንን በአመዛኙ ወደ አቅርቦት ተኮር የመሸጋገሩ ሥራ በስፋት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

በግብርና መስክ ባለፈው ዓመት ትኩረት ሰጥተን ከሠራንባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ ነው። በዚህ ረገድ የ2010/2011 ምርት ዘመን የሰብል ምርትን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 316 ሚሊዮን ኩንታል ማለትም 78% ለማምረት ተችሏል። ይህም በ2009/2010 ከተመረተው 267 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነፃፀር የ4.29 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የእርሻ ግብአቶችን በሚፈለገው መጠንና ወቅት ማቅረብ ሲሆን በዚህ ረገድ በክልሎች ፍላጎት መሠረት ለ2011/12 ምርት ዘመን የሚያስፈልግ አንድ ነጥብ ሁለት ሰባት (1.27) ሚሊየን ቶን የኬሚካል ማዳበሪያ የውጪ ግዥ በማከናወን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ደርሷል። ሀገራዊ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትና በዓመት ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ድሬዳዋ ላይ ለማቋቋም ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ሽርክና (Joint venture) በመፈራረም ሥራው በቅርቡ ይጀመራል።

በግብርናው ዘርፍ የ2011/12 በጀት ዓመት ዋናዎቹ የትኩረት መስኮቻችን አምስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡ የገበያ መር ግብርና (የሰብልና እንስሳት) ልማት ማስፋፋት፣ የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ አቅርቦትና ግብይትን ማጠናከር፣ ከውጪ የሚገቡ የግብርና ምርቶች በተለይም የስንዴ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት፣ በተለይም የስንዴ ምርት፣ የ5 ቢሊዮን ሀገራዊ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ማስተባበር እና ግብርናችንን ለማዘመን መስኖና የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፋት ናቸው። እነዚህንም ለማሳካት እንዲቻል ለኤክስቴንሽን ባለሞያዎችና ለአርሶና ለአርብቶ አደሮች ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የክህሎት ሥልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ ግብርናን በማዘመን አስፈላጊ የቀረጥ ማበረታቻ በማድረግ አርሶ አደሩ የዘመናዊ እርሻ መሳሪያዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት ይደረጋል፡፡

መሠረተ ልማትን በተመለከተ በ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሁለት ዓይነት የውኃ አቅርቦት ማለትም የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የመስኖ ውሃ አቅርቦት ለማሳካት ታቅዷል፡፡

የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን በገጠርና በከተማ ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዟል፡፡ በገጠር ወደ ሃምሳ ሺ የሚጠጉ አዳዲስ የውሃ ተቋማት ግንባታና ከአስራ ሦስት ሺ በላይ የማይሠሩ ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራ ይከናወናል፡፡ በከተማ ደግሞ 60 የመጠጥ ውሃ ተቋማት ጥናቶችን፣ 60 አዳዲስ ግንባታዎችንና 30 የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለማካሄድ ታቅዷል። በተመሳሳይም በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ፣ እንደ ሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም በመሳሰሉት ላይ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳካት ዕቅድ ተይዟል።

ከውሃ ጋር በተያያዘ ሌላው ትኩረት የመስኖ ውኃ አቅርቦት ነው፡፡ ቀደም ብለው የተጀመሩ እንደ ርብና ጊዳቦ ግድቦች ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሲሆን የዛሪማ ሜይ፣ አርጆ ደዴሳ እና መገጭ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። የመስኖ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ከሚሠራበት መጠን ወረድ ብሎ በአነስተኛ ደረጃ በብዛት እንዲከናወን ማስቻል አንዱ የመንግሥት ትኩረት ነው፡፡ በአነስተኛ ደረጃ ነገር ግን በብዛት እንዲከናወን የታሰበው የመስኖ ሥራ ዓላማው ሁለት ነው፡፡ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ምርታማነት ለማሳደግ፡፡

በዚህም መሠረት ተግባሩ በተጀመረባቸው ሦስት ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ማሠማራት የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ ይቀጥላል። በአጠቃላይ 34 ፕሮጀክቶች በተለያየ ደረጃ የሚጀመሩ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ አሥራ ሁለት ሺ (12,000) የተማሩ ወጣቶችን የሚይዝ የመስኖ ልማት እና የመስኖ ልማት አቅም ግንባታ ተግባራዊ ይደረጋል።

መልማት የሚችል ሰፊ ለም መሬት፣ መሥራት የሚችል የሰው ኃይል እና ለሌላም የሚተርፍ የውኃ ሀብት ይዘን ስንዴ ከውጭ እያስገባን ያለንበትን ሁኔታ ለማስቀረት የመስኖ ልማት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በሰፊው ትኩረት ይደረግበታል። እንዲሁም ከአርብቶ አደር አንፃር የተጀመሩ ልማቶችን አጠናክሮ በመቀጠል የቆላማ አካባቢዎችን አደጋ የመቋቋም አቅም የመገንባት ተግባራት ይከናወናሉ።

የኃይል አቅርቦት በተመለከተ መላው ሕይወታችንን የተቀላጠፈ በማድረግ በምርታማነት ላይ ያለውን ሰፊ አዎንታዊ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት የኃይል ተደራሽነትና አለመቆራረጥ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ይደረጋል። በዚህም ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው እንዲፋጠን ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚሠሩት 10 ፕሮጀክቶች ሥራቸው ይጀመራል። የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቱን ከማስፋትና ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ በአራት መቶ አምስት የገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮች አንድ ሚሊዮን ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል። የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስም በተሻሉ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች እንዲተዳደር ማድረግን ጨምሮ የመሥመር ማሻሻያዎች፣ የትራንስፎርመሮችና የቆጣሪዎች ምርመራና ማሻሻያዎች በሰፊው ይሠራሉ።

የኢንፎርሜሽና ኮሙኒኬሽን ቴክሎጂ በተመለከተ በዓለም ላይ ካለው ሀብት ከ65% በላይ የሚሆነው የሚመነጨው ከአገልግሎት ዘርፍ ሆኗል፡፡ በሀገራችን ከአገልግሎት ዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ ለማሳደግና በቴክኖሎጂ እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎች የጸደቁና በመጽደቅ ሂደት ላይ ያሉ በመሆናቸው በያዝነው ዓመት በርካታ የኢ-ኮሜርስ ጥረቶች ፍሬ የሚያፈሩበት ይሆናል።

ቁልፍ የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማዕከላትን በተሻለ የኢንፎርሜሽና ኮሙኒኬሽን (ICT) መሠረተ ልማትን የሚያስተሳስር፣ እንዲሁም ለ14 ዓመታት በሥራ ላይ ያለውን የወረዳ -ኔት መሠረተ ልማት የሚያዘምንና የመንግሥትን የዲጂታል ሥርዓት አስተዳደር ተጠቃሚነትን በእጅጉ የሚያሻሽል የሀገር አቀፍ የአይ.ሲ.ቲ አውታር ፕሮጄክት ዝግጅት ተጠናቆ የግል ዘርፍ በሚሳተፍበት መልኩ እየተሠራ ይገኛል። ይህ መሠረተ ልማት በዘንድሮው የበጀት ዓመት ሲተገበር አጠቃላይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች የጊዜን፣ የሀብትንና የሰው ኃይል ብክነትን ከመቀነስ አኳያ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳተላይት በያዝነው ዓመት በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም. በቻይና ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ወደ ጠፈር የሚላክ ሲሆን ይህ ሳተላይት ለግብርና፣ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የሳተላይት መረጃዎች ለመቀበል ይውላል። ይህንን ሳተላይት በራሳችን ባለሞያዎች የምንቆጣጠርበት ጣቢያም እንጦጦ በሚገኘው የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩቱት ግቢ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገት የጀርባ አጥንት ዘመናዊና ብቁ ተቋማትን መያዝ በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም የተሠማራበትን ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለ ሥልጣን መሥሪያ ቤት በአዋጅ የተቋቁመ ሲሆን የግሉ ዘርፍ በሀገራችን የቴሌኮም ዘርፍ ተዋናይ መሆን የሚችልባቸውን ሁኔታዎችን በማመቻቸት በያዝነው የበጀት ዓመት ሁለት ተጨማሪ የቴሌኮም ኦፐሬተሮችን አወዳድሮ ፈቃድ በመስጠት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ሦስት የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ይኖሩናል።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

2012 ዓ.ም. አዲሱን የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሚጀመርበት ዓመት ነው። የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዋና ዓላማዎቹ ትምህርትን በሁሉም መስክ ማዳረስ እንዲሁም የትምህርትን ጥራትና ብቃት መጨመር ናቸው። ትምህርትን ለማዳረስ የምንሠራው ሥራ ጥራትና ብቃቱን የሚቀንስ መሆን የለበትም። ለጥራት የምናደርገው ጥንቃቄና ጥረትም መስፋፋቱን የሚገታ መሆን የለበትም። በሁለቱ መካከል ያለውን ሚዛናዊነት ማስጠበቅ የአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ዋና መርህ ነው።

ተማሪዎች ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በሚገባ አውቀው፣ መብትና ግዴታቸውን ተረድተው ፣ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ በዕውቀት እንዲታነጹ ማድረግ ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሚጠበቅ ነው። ለዚህ ደግሞ አምስቱ የትምህርት ስኬት ተዋንያን፣ ማለትም ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ የትምህርትና ምርምር ተቋማትና መንግሥት በጋራ ለአንድ ዓላማ መሥራት አለባቸው።

እድገትና ብልጽግናን ያለ ዕውቀትና ምርምር ማስገኘት አይቻልም። ትምህርትን ማብቃት ሀገርን ማበልጸግ ነው። መንግሥት ለትምህርት ሥርዓቱ ስኬት በተቋም ግንባታ፣ በትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ የሚደረጉ የትምህርት ሥርዓቱ ተዋንያንን በሚቻለው ሁሉ ያበረታታል፤ ይደግፋል። በሌላ በኩል የትምህርትን ሰላማዊ ሂደት ለማወክ የሚካሄዱ አፍራሽ ተግባራትን ለሀገር ብልጽግናና ትውልድን ለመታደግ ሲባል አይታገሣቸውም።

ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና በሁለም ደረጃዎች ማስፋፋት እንዲቻል በ2012 ዓ.ም የተጀመረውን የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ወደ ተግባር የማስገባት ሥራዎች ይሠራሉ። የተጀመረው ረቂቅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ እንዲሁም የትምህርት ሕግ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል። ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በፍኖተ ካርታው የለውጥ ሐሳቦች መሠረት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሙከራ ትግበራ ለመጀመር እንዲቻል በ2012 ዓ.ም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ሁሉ እንዲከፈቱ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ይገባሉ።

የቴክኒክና ሞያ ትምህርትና ሥልጠናን በተመለከተ በመለስተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሠለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ሥራውን በማጠናከር የተለያዩ የሞያ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ የሚደረግ ሲሆን በፍኖተ ካርታው የለውጥ ሐሳቦች መሠረት በዚህም ዘርፍ የለውጥ ሥራዎች በ2012 ዓ.ም የሚሠሩ ይሆናል። የከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ በፍኖተ ካርታው የለውጥ ሐሳብ መሠረት በዚህ ዓመት የአንደኛ ዓመት ትምህርት እንዲጀምር ይደረጋል፤ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍንና ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተጠናከረ ሥራ ይሠራል።

የጤና ዘርፉ የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች አራት ናቸው። እነርሱም የወረዳ ትራንስፎርሜሽንን ማሳለጥ፣ ሆስፒታሎቻችንን ‹ያገባኛል (I care)› በሚል መርሕ አገልግሎታቸውን ለጤና ባለሞያዎችና ለሕሙማን በሚመጥኑ መንገድ ማደራጀት፣ ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል ያለው የጤና አገልግሎት (essential health service package)፣ እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምንና የሴቶች የልማት ቡድንን አሠራር ማሻሻል ናቸው።

የወረዳ ትራንስፎርሜሽንን ለማሳለጥ በሁለት ዘርፍ የሚካሄድ የማሻሻያ ፕሮግራም ይኖራል። ይኼውም የወረዳ የጤና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራምና ባለ ብዙ ዘርፍ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ናቸው። የወረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በጤና ሚኒስቴር በኩል የሚከናወን ሲሆን፣ ባለ ብዙ ዘርፍ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ደግሞ የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሚያካትት ፕሮግራም ነው።

ሆስፒታሎቻችንን ለሕሙማንና ለጤና ባለሞያዎች በሚመጥን መልኩ የማሻሻያ ፕሮግራሙ ‹ያገባኛል› በሚል መርሕ የሚከናወን ነው። በ24 ሆስፒታሎች በዚህ ዓመት የሚመጀረው ይህ ፕሮግራም ሆስፒታሎችንን በማሻሻል፣ በማዘመንና ደረጃቸውን በማሳደግ ላይ የሚያተኩር ነው።

ሦስተኛው ማሻሻያ ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል የሚደርሰው የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ይመለከታል፡፡ ይህኛው ከዚህ በፊት የነበረውን ማዕቀፍ ፈትሾ በማሻሻል በአዲስ የአሠራር ማዕቀፍ የሚተካ ፕሮግራም ነው። ከእርሱ ጋር ተያይዞ የሚመጣውና አራተኛው ክፍል ደግሞ ላለፉት ዓመታት ሲያገለግል የኖረውን የጤና ኤክስቴንሽንን በአዲስ አሠራርና አደረጃጀት መተካት ነው። ይህም የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሚባል ነው።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግና ብሎም የጾታ እኩልነት ማረጋገጥ ረጅም ጉዞ ላይ ከፍተኛ ቦታ የሚይዝ ግኝት በ2ዐ11 ዓ.ም ተመዝግቧል፡፡ ይህንን በመጠቀም በ2ዐ12 ዓ.ም እነዚህ ግኝቶች ጽኑ መሠት እንዲኖራቸውና እንዲሰፉ የማድረግ ተግባር ልዩ ትኩረት የሚሻ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ሴቶችንና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር በ2012 ዕቅድ ዘመን በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በህብረት ስራ ማህበራት እንዲደራጁ፣ የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ እና የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በዚህም የመስሪያ ካፒታል እና የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎች በማዘጋጀት የስራ ዕድሎች ይመቻቻሉ፡፡ በሂደትም በአገሪቱ በየደረጃው በሚደረጉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማሳተፍ እንደ ሀገር ለሚደረገው የድህነት ቅነሳ ትግል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሴቶችና የወጣቶች የኢኮኖሚና የፖለቲካ አጀንዳዎች በሁሉም ሴክተሮች እንዲካተቱና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መልኩ እንዲፈጸሙ ክትትል የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡

የባሕልና የቱሪዝም ሀብቶቻችን ለሠላም፣ ለአንድነትና ለብልጽግና የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ብዙ መልኮች ያሉት የዳበረ ባሕል አለን፡፡ ባሕላችን፣ እምነታችንና ተፈጥሮ የሰጡን ተዝቆ የማያልቅ የቱሪዝም ጸጋ አለን፡፡ እነዚህን የባሕልና የቱሪዝም ሀብቶቻችንን ለሕዝቦቻችን አንድነትና ሠላም፣ ለሀገራችንም ኢኮኖሚ በሚገባ መጠቀም አለብን፡፡

በ2012 ዓም የበጀት ዓመት በባሕል ዘርፍ ለእደ-ጥበብ ዘርፍ የአቅም ግንባታና የገበያ ትሥሥር ሥራ ለመሥራት፣ ኪነ ጥበብ ለሀገር ሠላም ግንባታ የሚውልበትን አሠራር ዘርግቶ ለመተግበር ታቅዷል፡፡ ከቅርስ ጥገናና እንክብካቤ አንፃር የላሊበላ፣ የአክሱም፣ የአባ ጅፋርና የጎንደር አብያተ መንግሥት ቅርሶች ጥገና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል፡፡ የሕዝቡ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ለሠላም፣ ለሕዝቦች አንድነትና ለባሕል ልውውጥ እንዲያገለግሉ ለመሥራት ታቅዷል፡፡

ከቱሪዝም ዘርፍ አኳያ የመስሕብ ልማት ሥራን ቅድሚያ በሚሰጣቸው የቱሪስት መዳረሻዎች ለማከናወን፣ ቱሪዝም ኢንቨስትመንትን ለማጎልበትና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ፣ የመስተንግዶ ተቋማት የአገልግሎት ጥራትና ደረጃን ለመከታልና ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማጎልበት እንዲሁም ዘመናዊ የቱሪዝም መረጃ ሥርዓት ዝርጋታን በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ታቅዷል፡፡

በስፖርት ዘርፍ መንግሥታዊና ሕዝባዊ የስፖርት አደረጃጀቶችን በማጠናከር ስፖርቱን በብቃት እንዲመሩ ለማስቻል፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ስፖርትን ወይንም ማስ ስፖርትን ለማስፋፋት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለማስፋፋትና ያሉትንም ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማድረግ፣ ስፖርታዊ ጨዋነትና ሰላማዊ ውድድር የሚረጋገጥበትን ሁኔታ ለይቶ ለመሥራት ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በተለይም በስፖርት ሜዳዎች እየተስተዋለ ያለውን ህገ ወጥነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሥራትና ሕግን በአጽንዖት በማስከበር የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን ከሜዳዎቻችን ላይ ለማጥፋት ታቅዷል፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች

በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል። ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተላችን በተለያዩ ሀገራት በእስር እና በእንግልት ላይ የነበሩ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሥራ ሥምሪት ስምምነቶችን መደራደርና ከተወሰኑት ጋር ስምምነትን ማጠናቀቅ ተችሏል። ከኤርትራ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የአየር ትራንስፖርት ያስጀመርን ሲሆን ያለን ግንኙነት በሕጋዊ ማዕቀፎች እንዲመራ ለማድረግ ድርድርና ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

ከጎረቤት ሀገራትና ከሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ጋር ቀስ በቀስ እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ጥምረት ለመፍጠር የሚያግዙ የነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቶች እና ያለ ቪዛ ወደ ሀገር ውስጥ መግባትን የመፍቀድ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ግንኙነት መስኮች በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን በዚህም ግንኙነቱን የማጥበቅ፣ ከአዳዲስ ሀገራት ጋር ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለመጀመር ተችሏል።

በያዝነው ዓመትም የውጭ ግንኙነታችን በዋነኝነት በአምስት መሠረታዊ ዕሳቤዎች የሚመራ ይሆናል። እነዚህም – ከዚህ በፊት በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ያገኘነውን መልካም ውጤት የማሳደግ፣ – በመግባባትና ትብብር መርሕ ላይ መመሥረት፣ – ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም፣ – ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ ፖሊሲን መከተል፣ – የውጭ ግንኙነቶቻችን ብሔራዊ ክብራችን እና የዜጎቻችን ክብር የሚያስጠብቅ እንዲሆን ማድረግ ናቸው። ይህን እውን ለማድረግም ጠንካራ አስፈጻሚ ተቋም፣ ብቁ ባለሞያዎችና የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎች ይሠራሉ።

የውጭ ግንኙነት መርሃችን ፉክክርንና ትብብርን ባማከለ መልኩ እንዲከናወን ታስቧል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን አሸናፊ ሆኖ መውጣትም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የውጭ ግንኙነታችን በውስጥ ጥንካሬያችን ላይ ይወሰናል፡፡ ጠንካራ አንድነት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓትና ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ሲኖረን የውጭ ግንኙነታችንም በዚያው ልክ ጠንካራ ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፍ መስኮች ተፎካካሪ ኃይል ሆነን ለመውጣትም እንችላለን፡፡

የተፎካካሪነት ብቃታችን ብቻውን የውጭ ግንኙነት ሥራችንን ስኬታማ አያደርገውም፡፡ ተፎካካሪነት ብቻውን አሉታዊ ገጽታ ስለሚኖረው፡፡ ለዚህ ነው ትብብር የሚያስፈልገን፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ እስከ ሩቅ ምሥራቅና ሩቅ ምዕራብ ሀገራት ድረስ የጋራ ጥቅሞቻችንንና ክብሮቻችንን ባስጠበቀ መልኩ ተባብረን ለመሥራት ዝግጁ ሆነናል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ድምጻችን ተሰሚና ወሳኝ የሚሆነው በትብብር ከሌሎች ወዳጆቻችን ጋር ስንደምራቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡

በአጠቃላይ የ2012 ዓም የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ ማሻሻያዎቻችንን ሥር የምናስይዝበት፣ ሀገራዊ አንድነታችንንና ሰላማችንን የምናጠናክርበት፣ የሕግ ማስከበር ሥራዎቻችንን መሬት የምናወርድበት፣ የዜጎቻችንን ክብርና ብሄራዊ ክብራችንን የምናስጠብቅበት፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቻችንን በመተግበር ፍሬ ማፍራት የምንጀምርበት፣ የጾታ እኩልነትና የወጣቶች ተሳትፎን የምናሳድግበት በባሕል በቱሪዝምና በማኅበራዊ ዘርፎች የያዝናቸውን ሕዝብ ተኮር ፕሮግራሞቻችንን የምንተገብርበት የበጀት ዓመት ይሆናል፡፡

ያለፉ ስህተቶችን በማረም፤ ባለፉት ዘመናት ባካበትናቸው ሀብቶቻችንና ጸጋዎቻችን ላይ በመመሥረት፣ አዳዲስ ፍላጎቶቻችንን በማካተት፤ በሁሉም መስክ ሀገራችንን አንድ እርምጃ ወደፊት የምናራምድበት ዓመት ይሆናል፡፡ ከፊታችን የሚጠብቁንን ታላላቅ ሀገራዊ ክስተቶች በሠላም፣ በአንድነት፣ በጨዋነትና በብቃት በመፈጸም የኢትዮጵያን ታላቅነት የምናስመሰክርበት ዓመት ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሁላችንንም የነቃና የበቃ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡

በሀገራችን ከመጣው ለውጥ ሂደት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን ይሁንታ የተገኘባቸው እመርታዎችን ያገኘነውን ያህል የምር ትኩረት ሰጥተን መነጋገር የሚገባን ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ይህም ነገ የሁላችንም የእኩል ቤት የሆነች ሀገር ለመፍጠር ላለን ፍላጎት እና ለያዝነው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ጉልበት የሚያጎናጽፍልን ይሆናል፡፡

በምናያቸውና በምንሰማቸው አስደሳች ነገሮች እንደምንደሰተው ሁሉ በዚህ ሀገር የሚሆነውን ክፉ ተግባር መጠየፍ፤ ተመልሶም እንዳይደገም አስተዋጽዎ ማበርከት የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን የግድ ልንሳተፍበት የሚገባ የሀገር ግንባታ ጉዞ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት የሁላችንም ራስ ምታት መሆን አለበት፡፡

አልፎ ሂያጅነት ማለትም በሁሉም ነገር አይመለከተኝም ብሎ ማሰብ፣ እንግድነት፤ ባይተዋርነት እና ምንአገባኝነት ለሀገር ዕድገት አይበጁም፡፡ ችግር ሲከሠት ሁላችንንም አይምርም፡፡ የሚሻለው በባለቤትነት ስሜት በተነሣሽነት መሥራት ነው፡፡ ማንም አያገባኝም ሊል፤ ማንም ባይተዋር ሊሆን አይገባውም፡፡ የአንዱ ህመም ሌላውንም ሊሰማው ይገባል፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ያስተማሩን የሰብዓዊነት፤ የመደጋገፍ እና ችግርን በደቦ የማሸነፍ መልካም እሴታችን ነው፡፡ ሁላችንም የሀገራችን ባለቤቶች ነን፡፡ ምትክ ለሌላት ሀገራችን ዕውቀታችንን፣ ጉልበታችንን፣ ሀብታችንንና ቀና ልቡናችንን ሁሉ ይዘን እንነሣ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡