የደህንነት ተቋማትን አቅም የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ ነው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

93
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 26/2012 መንግስት የደህንነት ተቋማት የማነፍነፍ አቅማቸው እንዲያድግና ችግር ሲከሰት በአጭር ጊዜ የማስቆም አቅማቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ የአቅም ማሻሻያ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት ዛሬ የተጀመረውን የህዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ነው። ፕሬዚዳንቷ በዚሁ ንግግራቸው በተያዘው በጀት ዓመት “የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን የሕጋዊ ማዕቀፎችና አቅሞችን በማዳበርና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ አሁን በሀገራችን ያለውን አንጻራዊ ሠላም ወደ አስተማማኝ ሠላም ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል።" ብለዋል። በዚህም በተለይ የፌደራል ፖሊስ ብቁ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ጥናት ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል። "በሂደቱም የአመራርና የህግ ማዕቀፎችን ለማሻሻል በአጭር ጊዜ በጠንካራ አስተምህሮ የሚመራ ጠንካራ የህግ አስከባሪ አካላት ይኖረናል" ሲሉም ተናግረዋል። የክልል የፀጥታ አካላትም አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑም ነው የገለጹት ፕሬዚዳንቷ። የአገር መከላከያ ሰራዊቱ የሙያ አቅም የላቀ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል። በቀጣይ አገሪቱ የምታስተናግዳቸውን አገራዊ ምርጫና ሌሎች ክስተቶች ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ይፈጠራል ሲሉም ተናግረዋል። መንግስት የአገሪቱን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ከተለያዩ የህብረተሰብ አደረጃጀቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገልጸዋል። የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ዋናው ባለቤት ህዝብ በመሆኑ ዘላቂ ሰላምን በመገንባትና ህግን በማክበርና በማስከበር ረገድ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ፕሬዚዳንቷ አክለውም “ኅብረተሰብ ተኮር የሠላም ግንባታ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ፤ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብሎም ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትም ይከናወናሉ። ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብ ልማት ፕሮግራሞችም ይካሄዳል።” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም