ለዜጎች ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የግሉ ዘርፍ መጠናከር ወሳኝ ነው- የጤና ሚኒስቴር

62
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 26 /2012 ለዜጎች ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የግሉ ዘርፍ መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። አራተኛው የአፍሪካ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በጉባኤው መክፈቻ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት የዜጎችን የጤና አገልግሎት ለማሻሻልና ተደራሽነቱን ለማሳደግ  በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላቶች  ቅንጅት ወሳኝ ነው። በብሄራዊ ደረጃ የተያዘውን የጤናው ዘርፍ ዕቅድ ለማሳካት ከመንግስት የጤና ተቋማት ባለፈ በዘርፉ የተሰማሩ የግል ተቋማት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል። አገሪቱ ከሚያስፈልጋት አጠቃላይ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ከውጭ እንደሚገባ የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታዋ ይህንን በአገር ውስጥ ለመተካት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለሃብቶች  ያስፈልጋሉ ብለዋል። በተለይ በውጭ አገር ድጋፍ በመንግስት ጤና ተቋማት ብቻ በነጻ የሚሰጡ አገልግሎቶችም በግል ዘርፉ እንዲሰጥ መንግስት ፍላጎት ያለው መሆኑን ዶክተር ሊያ አመልክተዋል። በአገሪቱ እየተበራከተ በመጣው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና ማከም ላይ የግሉ ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ መንግስት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነውም ብለዋል። ዶክተር ሊያ እንዳሉት መንግስት ከግሉ ዘርፍ  ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር በርካታ እቅዶች ነድፎ እየሰራ ነው። ጉባኤው በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በስፋት በዘርፉ እንዲሰማሩና በአገሪቱ ያለውን መልካም አጋጣሚ እንዲያዩ ያግዛቸዋል ብለዋል። የልምድ ልውውጡም በአገሪቱ በዘርፉ ከ25 በመቶ ያልዘለለውን የግል ባለሃብት ተሳትፎ ያሳድገዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ዘለቀ እንዳሉት ጉባኤው በዘርፉ የተሰማሩ የአፍሪካ አገራት ልምድ የሚለዋወጡበት ነው። በተለይ በመንግስታት በቂ ድጋፍ ያልተሰጠውን የግሉ ዘርፍ ድጋፍ እንዲያገኝ በጋራ የሚመክሩበት መሆኑንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት የሚደረገው ድጋፍ የተሻለ ቢሆንም አሁንም በመሬት አቅርቦት መንግስት በሚሰጠው ማበረታቻና በሌሎችም ከፍተት እንዳለ ጠቁመዋል። የአፍሪካ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር አሚር ታከር በበኩላቸው በአፍሪካ በጤናው ዘርፍ የግልና የመንግስት ቅንጅት የሚፈለገው ደረጃ አልደረሰም። ይህ ደግሞ በጤናው ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ ማድረስ አልተቻለም። በጉባኤ የሚካሄደው የልምድና የእውቀት ልውውጥ ፖሊሲ አውጪዎች ለግሉ ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችው አራተኛው የአፍሪካ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ ለሶስት ቀናት ይቆያል። በጉባኤ ከ50 ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ከ350 በላይ ሰዎችና ከ9 አገራት የተወከሉ የጤና ሚኒስትሮች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም