በሀዋሳና ወላይታ ሶዶ የተነሱትን ግጭቶች በውይይት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ስፍራው ያቀናሉ

124
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሀዋሳና ወላይታ ሶዶ ከተሞች የተነሱትን ግጭቶች ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ገለጹ፡፡ በስፍራው ተገኝተው ውይይት እስኪያደርጉ ድረስ በሰላምና ፍቅር የሚታወቀውና የትንሿ ኢትዮጵያ ማሳያ የሆነው የደቡብ ክልል ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ለአካባቢያቸው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ የጸጥታ አካላትም ህብረተሰቡን ባሳተፈና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ክልል እንሁን' በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱ ስርዓት ያስቀመጠ በመሆኑ ሁሉንም ነገር በሰላማዊ መንገድ መጠየቅና ማስተናገድ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ከወሰን ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥናት መመለስ ይቻል ዘንድ ይህንን የሚከታተል ኮሚሽን ለማቋቋም መንግስት እያሰበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሚቋቋመው ኮሚሽን ከየአካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎችን በመቀበል ስር ነቀል መፍትሔ እንደሚሰጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም