በአማራ ክልል በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 56 ተማሪዎች ሽልማት ተሰጠ

66
ባህር ዳር ኢዜአ  መስከረም 24 / 2012-በአማራ ክልል የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈተና ወስደው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 56 ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተ። ለተማሪዎቹ የቁሳቁስና የገንዘብ የማበረታቻ ሽልማት የተሰጠው በክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ በበፕሮፌሰር አስራት ወልደየሱስ ስም በተቋቋመው አስራት የትምህርት ሽልማት ድርጅትና በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም አማካኝነት ነው። በባህር ዳር ግራንድ ሆቴል ዛሬ በተዘጋጀው የሽልማት መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ  የላቀ ውጤት በማምጣት ለሀገራችውና ለክልሉ ኩራት የሆኑ ተማሪዎች ለሽልማት መብቃታቸውን ተናግረዋል። በ2011 የትምህርት ዘመን በክልሉ አጠቃላይ ከተፈተኑ 92 ሺህ በላይ ተማሪዎች ውስጥ 55 ሺህ 158 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ  ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባታቸውን ተናግረዋል። "ከነዚህ መካከልም 51 ተማሪዎች 600 እና ከዚያ በላይ ውጤት በማምጣታቸው በክልሉ ታሪክ  ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል" ያሉት ዶክተር ይልቃል፣ ከነዚህ ውስጥም 13ቱ ሴቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት። አስራት የትምህርት ሽልማት ድርጅት ከዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር በመተባበር ከአጠቃላይ ተሸላሚዎች መካከልም ለ23ቱ  ለእያንዳንዳቸው የላብቶፕ ሽልማት ተበርክቷል። ሁለት አይነስውራንን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለእያንዳንዳቸው የ5 ሺህ ብር ሽልማት ማበርከቱን ዶክተር ይልቃል አስረድተዋል። ተሸላሚ ተማሪዎቹ በቀጣይም በዩኒቨርሲቲ ቆይታችው የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ ተቋቁመው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ሀገርና ቤተሰባቸውን ለማገዝ ከወዲሁ እንዲዘጋጁም አስገንዝበዋል። "አስራት የትምህርት ሽልማት ድርጅት ከክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር በመተባበር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የላብቶፕ ሽልማት ማበርከቱ ያስመሰግነዋል" ብለዋል ዶክተር ይልቃል ። የአስራት የትምህርት ሽልማት ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶክተር ኃይለማርያም አወቀ በበኩላቸው ድርጅቱ በክልሉ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ላብቶፕ ሲሸልም ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ መሆኑን ነው የገለጹት። ድርጅቱ በታዋቂው የክልሉ ተወላጅ ፕሮፌሰር አስራት ወልደኢየሱስ ስም ከአንድ ዓመት በፊት በጎ ፈቃደኛ በሆኑ ምሁራን አማካኝነት መቋቋሙን ጠቁመው፣ ሽልማቱ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ለማበረታታት ታስቦ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ በ2010 የትምህርት ዘመን በ12 ተማሪዎች የጀመረውን ሽልማት በቀጣይም የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ የክልሉ ተማሪዎችንና መምህራንን በመሸለም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። "የተበረከተልኝ የላብቶፕና የገንዘብ ሽልማት ለበለጠ ድል እንድነሳሳ ትልቅ ስንቅ ሆኖኛል" ያለችው ደግሞ ከባህር ዳር ኤስ.ኦ.ኤስ ትምህርት ቤት 631 ውጤት በማስመዝገብ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ዳግማዊት በድሉ ናት። "የምፈልጋቸውን አጋዥ የትምህርት ቁሳቁሶች በማቅረብ ለዚህ ውጤት እንድበቃ እናትና አባቴ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ" ብላለች። በቀጣይም የሕክምና ትምህርቷን በርትታ በመከታተል የቤተሰቦቿን ወረታ ለመክፈልና ሀገርና ወገንን ለማገልገል ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ተናግራለች። በሀገር አቀፍ ደረጃ 645 ውጤት በማምጣት አንደኛ የሆነው ከባህር ዳር አየለች ደገፉ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸላሚ የሆነው ብሩክ ዘውዱ ነው። "የተሰጠኝ ሽልማት ተደራራቢ ኃላፊነት መሆኑን ስለምረዳ በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርቴን በመከታተልና የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የክልሌን ስም ዳግም ለማስጠራት ጠንክሬ ዕስረላሁ" ብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም