የሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመር ግንባታ እንዲቀጥል አማራጭ የውሳኔ ሀሳቦች ቀርበዋል

51
መቀሌ (ኢዜአ) መስከረም 24 ቀን 2012 በበጀት እጥረት ምክንያት ግንባታውን የተቋረጠው የሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመር ግንባታ እንዲቀጥል ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማራጭ የውሳኔ ሀሳቦችን ማቅረቡን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የፌደራል ትራንስፖርት ሚኒስትር ከክልል ቢሮዎች ጋር በመቀሌ ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄደው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል። በምክክር መድረኩ ላይ የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያና መቀሌ ያለውን የባቡር መስመር ግንባታ አፈጻጸምና ስለ ተቋረጠው የሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመር ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበው ሚኒስቴሩ ምላሽ ሰጥቶበታል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር በእዚህ ወቅት የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት የብድር አቅርቦት ተገኝቶለት ግንባታ መጀመሩን አስታውሰዋል። የሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ግን ብድር ይገኝለታል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ መንግስት የግንባታው ስራውን እንዳስጀመረው ተናግረዋል። የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ አፈጻጸም 80 ከመቶ መድረሱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት 54 በመቶ ከደረሰ በኋላ በበጀት እጥረት ምክንያት ግንባታው መቋረጡን ገልጸዋል። "ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግንባታው አፈጻጸም ከግማሽ በላይ የደረሰውን የሀራ ገበያ መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት መቀጠል እንዳለበት ውሳኔ ላይ ደርሷል" ብለዋል። በዚህም ፕሮጀክቱ የሚቀጥልበትን አማራጭ ሀሳቦች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነው ያስረዱት። የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ 392 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት ግንባታው እየቀጠለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበጀትና እቅድ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ሰሎሞን አያሌው ናቸው። በተያዘው ዓመት አፈጻጸሙን 90 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። አቶ ሰለሞን እንዳሉት ከሀራ ገበያ መቀሌ 216 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የባቡር መስመር የግንባታ ሥራ በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቢጀመርም አፈጻጸሙ 54 ከመቶ ላይ ደርሶ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ቆሟል። የውይይቱ ተሰታፊዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትራንስፖርት ፖሊሲ ሳይኖረው እየሰራ ነው፣ የመቀሌ ወልድያ ደሴ አዲስ አበባ መስመር የህዝብ ትራንስፖርት ተገድቦ እንዴት ዝም ተብሎ ይቀጥላል የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ሚኒስቴር ዴኤታዋ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እስካሁ ድረስ የትራንስፖርት ፖሊሲ ባይኖረውም በርካታ ስራዎች ከማከናወን አለመገደቡን ነው የገለጹት። ሚኒስቴር መስራቤቱ ፖሊሲ እንዲኖረው ያዘጋጀውን የመጨረሻ ረቂቅ ህግ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መላኩን ተናግረዋል። "የመቀሌ ወልድያ ደሴ አዲስ አበባ መስመር መንገድ ባለቤትነቱ የፌደራል መንግስት ቢሆንም ችግሩ እንዲፈታ ቅድሚያ የአማራና ትግራይ ክልሎች ውይይት አድርገው ችግራቸውን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል። የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ  ቤቱም ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ የድርሻውን ለመጫወት ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስርት ዴኤታዋ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም