የኢትዮ - ሩሲያ የትብብር ማዕቀፍ የፊታችን ጥቅምት ወር እንደሚፀድቅ ይጠበቃል

98
ኢዜአ/  መስከረም 23 /2012  የኢትዮጵያና የሩሲያ የትብብር ማዕቀፎች በጥቀምት 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የሩሲያ አፍሪካ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል። ከመስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሩሲያ ፒተርስበርግ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 7ኛው የኢትዮ-ሩስያ የጋራ ኮሚሽን ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል። የኢፌዴሪ ኢኖሼሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የላከው መረጃ እንደሚያመለክተው ጉባዔው አዳዲስ የትብብር ማዕቀፎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ በመድረስ ተቋጭቷል። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የጋራ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) የተመራ ነው። በፒተርሰበርግ ሲካሄድ የቆየው 7ተኛው የኢትዮ-ሩስያ የጋራ ኮሚሽን ጉባኤ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ቴክኒካዊና የንግድ ትብብር አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል። ሁለቱ አገራት ከሚፈራረሟቸው የመግባቢያ ሰነዶችና ስምምነቶች በተጨማሪ አዳዲስ የትብብር መስኮችን በመለየት በዝርዝር ውይይት እንደተደረገባቸውም ተገልጿል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የጋራ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በጉባኤው 11 አጀንዳዎች ቀርበው በስምንቱ ላይ የትብብር ውሎችና የጋራ መግባቢያ ሰነዶች ለሚመለከታቸው ተቋማት እንዲመለከቷቸው እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ የትብብር ማዕቀፎቹ ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም በሩሲያ ሶቺ ከተማ በሚካሄደው የአፍሪካ ሩሲያ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ይጽደቃል ተብሎ ይጠበቃል። በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የትብብር ኮሚሽኑ ጉባኤ የሁለቱን አገራት የጋራ ጥቅም በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ይከፍታል ብለዋል። ኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1898 ሲሆን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓል ባለፈው ዓመት እንዳከበሩ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2021 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ጉባዔ ለማስተናገድ ያላትን ምቹነት የሚገመግም ቡድን በአዲስ አበባ ባለፉት ቀናት ግምገማውን አካሂዷል። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ጉባዔ ለማስተናገድ የሚያስችላት አቋም ላይ መሆኗንም ተመልክቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም