12ኛው “የአውሮፓ ቀን” የህጻናት ሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሂዷል

4019

 

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2010 “የአውሮፓ ቀን” በማስመልከት የህጻናት ሩጫ ውድድር ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ለ12ኛ ተካሂዷል።

በየዓመቱ ግንቦት አንድ ቀን ለአሁኑ የአውሮፓ ህብረት መፈጠር መሰረት የሆነውን እ.አ.አ በ1950 የተፈረመው የጀርመንና ፈረንሳይ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ውህደት ስምምነት ታስቦ ይውላል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር አስተባባሪ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች 2ሺህ500 ታዳጊዎች ተሳትፈዋል።

ይህ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ1ሺህ500 ተወዳዳሪዎች ብልጫ አለው፡፡

ወደ ፌስቲቫልነት በሚያዘነብለው በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ታዳጊዎች ራሳቸውን ከማዝናናት ባለፈ ጤናማ እንዲሆኑ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ታዳጊ ህጻናት የሚያሳትፉ ውድድሮች እንደሚያዘጋጅ የገለጹት ወይዘሮ ዳግማዊት በየዓመቱ ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ ህጻናት ብቻ የሚካፈሉበት ውድድር እንዳለ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በተካሄዱት የአውሮፓ ቀን “የህጻናት ሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፉ ታዳጊዎችን የመመልመልና ብቁ ለማድረግ እስካሁን የተሰራ ነገር ባይኖርም በቀጣይ  ጥረት እንደሚደረግ ወይዘሮ ዳግማዊት ገልጸዋል።

ዘንድሮ የታላቁ ሩጫ፣ ቅድሚያ ለሴቶችና የሃዋሳ ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች መካሄዳቸውንና ሌሎች ውድድሮችም እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ሩጫ እንዲጀመር ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ይሄንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚሰራና በአፍሪካ ከሚካሄዱት የጎዳና ላይ ሩጫዎች የተሻሉ ውድድሮችን በብዛት ማዘጋጀት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ አክለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽህፈት ቤት የፕሬስና የመረጃ ኦፊሰር አቶ ሰለሞን ከበደ በበኩላቸው ህጻናት ላይ መስራት የወደፊት ተረካቢ ላይ መስራት እንደመሆኑ ተቋማቸው ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ውድድሩን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የታዋቂ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው ኢትዮጵያ ወደፊት ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንዲህ አይነት ውድድሮች መካሄዳቸው ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።

ውድድሩ የአውሮፓ ህብረትና ኢትዮጵያ ካላቸው ስትራቴጂካዊ ትስስር ዋነኛ ከሆኑት መካከል ወጣቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ የልማትና የኢኮኖሚ ተግባራት አካል እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ የተሳታፊዎችን ቁጥር በመጨመር ውድድሩን ይበልጥ ደማቅ ለማድረግ እንደሚሰራ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።

በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከአምስት ዓመት በታች የእድሜ ክልል ያሉ ታዳጊ ህጻናት 300 ሜትር፣ ከስምንት ዓመት በታች 800 ሜትር፣ ከአስራ አንድ ዓመት በታች 1ሺህ ሜትርና ከ14 ዓመት በታች 1 ሺህ 400 ሜትር ሮጠዋል።

ከአምስት ዓመት በታች ህጻናት 300 ሜትር ወንዶች ሰንበቶ አያሌው፣ ብሩክ ፈለቀና ተስፋዬ ዳኜ ከአንድ እስከ ሶስት ሲወጡ በሴቶች ትህትና በርሄ፣መነን ዮርዳኖስና ምስጋና በርተሎሚ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ከስምንት ዓመት በታች 800 ሜትር ወንዶች ያሬድ ነጋ፣ ተዋበ ንዋይ፣ ናኦል አብዮት በሴቶች አቢጌል ዳንኤል፣ ወንጌል ኤልያስና ሜሮን ፍስሀ ከአንድ እስከ ሶስት ወጥተዋል።

ከአስራ አንድ ዓመት በታች አንድ ኪሎ ሜትር ወንዶች አልአዛር ረዘነ፣ ካሌብ ዮናስና ቀነኒሳ ኡመር እንዲሁም በሴቶች ማህሌት ዘገየ፣ ኤደን ሳይመንና ሀያት ነስማን ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው ገብተዋል።

ከ14 ዓመት በታች 1 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር ወንዶች ኢማሁስ አሰፋ፣ ምንዳርአለው እሸቱና የአብስራ ሰለሞን ከአንድ እስከ ሶስት ሲወጡ በሴቶች መሰረት በቀለ፣ አስቴር አድማሱና ጢያ ጫላ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በውድድሩ  አሸናፊ ለሆኑ ህጻናት የዋንጫና የመጽሐፍ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በአጠቃላይ ውድድሩን ላጠናቀቁ ህጻናት የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚስተር ጆን ቦርግስታምና የሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ ፊርማ የሰፈረበት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።