በሰሜን ሽዋ ዞን ባለፉት ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የተሰበሰበ 4 ሺህ ዩኒት ደም ጥቅም ላይ ዋለ

52
ደብረ ብርሃን ሰኔ 8/2010 በሰሜን ሽዋ ዞን ባለፉት ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የተሰበሰበ 4 ሺህ ዩኒት ደም በአደጋ ለተጎዱና ለወላድ እናቶች ጥቅም ላይ መዋሉን የደብረብርሃን ደም ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። የደብረብርሃን ደም ባንክ አገልግሎት ዳታ ማናጀር ወይዘሮ መቅደስ መገርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰበሰበው ደም በትራፊክ አደጋ ለተጎዱ፣ ለወላድ እናቶችና ህጻናት ጥቅም ላይ በማዋል ህይዎታቸውን መታደግ ተችሏል። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበው ደም በዞኑ ለሚገኙ 11 ሆስፒታሎች በማከፋፈል ከ3 ሺ በላይ ሰዎችን መርዳት መቻሉን ገልፀዋል። በተለያዩ አደጋዎችና በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ህብረተሰቡ የጀመረው የደም ልገሳ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ አስከዚህ ዓመት መጨረሻም 4 ሺህ 800 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መካከል በደብረብርሃን ከተማ የ08 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉነሽ ታደሰ ደም መለገስ በጤንነታቸው ላይ ምንም አይነት ችግር እንደማያመጣ በጤና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ለስምተኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡ በየ3 ወሩ በሚሰጡት ደም ክቡር የሰው ህይወት መታደግ በመቻላቸው ውስጣዊ እርካታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ወይዘሮ ስርጉት አደናግር በበኩላቸው እስካሁን በግንዛቤ ክፍተት ስለሚፈሩ ደም ሳይለግሱ መቆየታቸውንና አሁን ጎረቤቶቻቸው በተደጋጋሚ ደም ለግሰው ምንም ችግር እንዳልደረሰባቸው በማረጋገጣቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላም በየ3 ወሩ ደም ለመለገስ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወይዘሮ ትግስት ወንድሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ደም በመለገሳቸው መደሰታቸውንና ጉዳት እንደማያደረስ በመረዳታቸው ልምዳቸውን ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ዓመት 2 ሺህ 693 ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ከደም ባንክ አገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም