የናይጄሪያው ፕሬዚደንት ሙሃመድ ቡሃሪ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊያቀኑ ነው

55
ኢዜአ መስከረም 21/2012 ፕሬዚደንት ቡሃሪ ለሶስት ቀናት ለሚቆይ የስራ ጉብኝት ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያቀኑ ቢቢሲ አስነበበ፡፡ ጉብኝቱም በደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የቀረበ ግብዣ እንደሆነና   ባሳለፍነው ወር በጆሃንስርግና ሌሎች የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ተነስቶ ከነበረው  የመጤ ጠል ጥቃት በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በናይጄሪያዊያን ደህንነት ዙሪያ በመወያየት ከአቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመገንባት የሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ናቸው፡፡ የናይጀሪያ መንግስት በመጤ ጠል ጥቃቱ የዜጎቼ የንግድ ቦታ ኢላማ ተደርጓል በሚል ፕሬዚደንት ቡሃሪ ወደ ደቡብ አፍሪካ ልዑክ መላካቸው የሚታወስ ሲሆን ናይጄሪያም በሁኔታው ላይ ያላትን ቅሬታ ለመግለፅ ሞክራለች፡፡ ፕሬዚደንት ቡሃሪ የናይጀሪያዊያን ፍላጎት ለማስጠበቅ የተቻለውን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን ለማሳየትም ዝግጁ እንደሆኑ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ወር በተፈፀመ የመጤ ጠል ጥቃት የናይጄሪያውያንን ጨምሮ የንግድ ሱቆች እንዲዘረፉ ምክንያት ሆኗል ፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ የናይጄሪያ ዜጎች ከደቡብ አፍሪካን በመውጣት ወደ ሃገራቸው ገብተዋል፡፡፡ በጉብኝቱ ወቅትም ፕሬዚደንት ቡሃሪ ደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ናይጀሪያዊያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የናይጀሪያው ፕሬዚደንቱንና ልዑካቸው የናይጀሪያ ንግድ ተወካዮችን ጨምሮ በንግድ መድረኩ ላይ በመገኘት በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት በማሰብ እ.አ.አ በ1999 የተቋቋመው የደቡብ አፍሪካ-ናይጀሪያ ቢአይ ብሄራዊ ኮሚሽን አማካኝነት ይመራልም ተብሏል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በአፍሪካ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ቢሆኑም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸው እየቀነሰ መጥቷልም ተብሏል፡፡ ሁለቱም መሪዎች የመጤ ጠል ጥቃት እንዲቆም የሚፈልጉ ሲሆን የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለመፍጠር እንደሚሰሩም መረጃው አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም