ከጎንደር ሆስፒታል የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ ለጤና ችግር ዳርጎናል--- የአካባቢው ነዋሪዎች

160
ጎንደር ሰኔ 8/2010 ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ የመኖሪያ ቤታቸው አካባቢን በመበከል ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደዳረጋቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የአካባቢው  ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ሆስፒታሉ በበኩሉ " የፍሳሽ ቆሻሻው የሚያስከትለውን የጤና ጉዳት ለመቀነስና ብሎም ለማስወገድ እየሰራሁ ነው" ብሏል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጎበዜ ሰጠኝ በሰጡት አስተያየት  " ከሆስፒታሉ በየቀኑ የሚለቀቀው የተበከለ ፍሳሽ ቆሻሻ ጉንፋንን ጨምሮ ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት የጤና ችግር ዳርጎኛል " ብለዋል፡፡ ለረጅም ዓመታት እያደረሰ ያለውን ብክለት እንዲቆም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን  አቤቱታቸውን ለሆስፒታሉና ለሌላም የመንግስት አካል  ቢያቀርቡም  መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ለጤና ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችና ለተላላፊ በሽታ የሚዳርጉ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ከሆስፒታሉ በየቀኑ እንደሚለቀቁ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ  ሁሉአገርሽ ታረቀኝ የተባሉት ነዋሪ ናቸው፡፡ "በሆስፒታሉ የፍሳሽ ቆሻሻ ባለቤቴና ልጆቼ በየጊዜው በጉንፋንና ቆዳ ላይ በሚወጣ ሽፍታ ለጤና ችግር ተዳርገዋል " ብለዋል፡፡ ወይዘሮ እናና በላይ በበኩላቸው ከሆስፒታሉ የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ የሚያልፍ በመሆኑ ለአስም በሽታ መጋለጣቸው ተናግረዋል፡፡ "ሆስፒታሉ ማህበራዊ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚለቀው ለጤና ጎጂ የሆነ የተበከለ የፍሳሽ ቆሻሻ ሊቆም ይገባል " ብለዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አካባቢ ጥበቃ መምሪያ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን ባለሙያ ወይዘሮ  ዳሳሽ ኡመር በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ የተበከለ የፍሳሽ ቆሻሻ ከቅጥር ግቢው በሶስት አቅጣጫ ወደ ውጪ እንደሚለቅ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ የፍሳሽ ቆሻሻው የህብረተሰቡን ጤና ከመጉዳት በዘለለ የጣና ሐይቅ ገባር ወደ ሆነው የቀሃ ወንዝ ጭምር ስለሚፈስ የሚፈጥረው የአካባቢ ብክለት ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ "ሆስፒታሉ የፍሳሽ ቆሻሻውን የአካባቢ ብክለትም ሆነ የጤና ችግር በማያስከትል መንገድ በአፋጣኝ ማስወገድ እንደሚገባው መምሪያው በደብዳቤ አሳውቋል" ብለዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ፍሰሃ አድማሱ የህብረተሰቡ ተወካዮች ከሆኑና ከዞብል ክፍለ ከተማ ስለ ሆስፒታሉ የፍሳሽ ቆሻሻ ቅሬታ መቅረቡን አምነዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር የሆነው የአስተዳደር ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግሮ ችግሩ እንዲፈታ ውሳኔ በማሳለፍ ጥናት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ችግሩን  የሚፈታበትን መንገድ ጥናት የሚያካሂደው አካል በሚያቀርበው የመፍትሄ ሀሳብ መነሻነትም በቅርብ ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰጥ ዳሬክተሩ አመላክተዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም