በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ ነው

93
ደብረ ብርሃን ሰኔ 8/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በሁለት ሺህ 755 ሄክታር የማሽላና በቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች የመካለከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ወርቁ ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 46 ቀበሌዎች በተዘራው የበቆሎና ማሽላ ቡቃያ ላይ ተምቹ ካለፈው ወር ጀምሮ ተከስቷል፡፡ ተምቹን ለመከላከል በተደረገው ጥረትም 3 ሺህ 480 አርሶ አደሮችን በለቀማ በማሳተፍና 900 ሊትር ኬሚካል በመርጨት እስካሁን  አንድ ሺህ 380 ሄክታሩን መከላከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በባህላዊ መንገድ የተካሄደው የመከላከል ስራ  ውጤታማ በመሆኑ አርሶ አደሩ ለቀማውን አጠናክሮ እንዲቀጥል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ተምቹ ከተሰከሰተባቸው ወረዳዎች መካከልም ቀወት፣ ኤፍራታና ግድም፣ ጣርማበር፣ አንኮበር፣ ሽዋሮቢትና አንፆኪያ ወረዳዎች ይገኙበታል። “እስካሁን በመኽር እርሻ በዘር ከተሸፈነው ከ22 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቆሎና ማሽላ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛልም'' ብለዋል፡፡ በቀወት ወረዳ የየለን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብይ ሀብቱይመር በበኩላቸው በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት የበቆሎ ሰብል በተምች በመጠቃቱ የምርት መቀነስ ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳለቸው ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ባለሙያዎች በመታገዝ በ8 ሊትር ኬሚካል ርጪትና ቤተሰባቸውን በማሳተፍ በባህላዊ መንገድ በመልቀም ለመከላከል ቢሞከርም ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንዳልቻለ ገልፀዋል፡፡ በዚሁ ወረዳ የብርብራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መካሻ በሻ በሩብ ሄክታር መሬት ላይ በዘሩት የቆሎና ማሽላ ማሳ ላይ ተምች በመከሰቱ በምርታቸው ላይ ጫና እንሚፈጥር ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ተምቹ ቡቃያ የበቆሎ ሰብልን በፍጥነት እንደሚያጠቃ ገልፀው ይህንኑ ለመከላከል ኬሚካልና በለቀማ ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዞኑ እስካሁን በዘንድሮው የመኸር እርሻ 509 ሺህ 816 ሄክታር መሬት ለማልማት የታቀደ ሲሆን እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ 22 ሺህ ሄክታር መሬት ፈጠኖ በሚዘራ ሰብል ተሸፍኗል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም