በወላይታ ዞን የትምህርት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ግብአቶችን የማሟላት ሥራ ተከናውኗል

56
ሶዶ ኢዜአ መስከረም 19/ 2012 - በወላይታ ዞን የትምህርት ዘመኑን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የትምህርት ግብአቶችን በማሟላት ወደስራ መግባቱን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ተፈሪ ላቢሶ ለኢዜአ እንዳሉት የ2012 ዓ.ም የትምህርት ስራን ውጤታማ ለማድረግ ማህበረሰቡን፣ አመራሩንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ከማህበረሰብ ተሳትፎና ከዞን አስተዳደር በተገኘ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ የቤተሙከራ ዕቃዎች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም ማጣቀሻ መጻህፍት ግዥና የቤተመጻህፍት ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል። በተላይም በፕላዝማ ትምህርት አሰጣጥ ላይ ይስተዋል የነበረውን መቆራረጥ ለማስቀረት ትምህርቶቹ የተጫኑባቸው ከ240 በላይ ኮምፒዩተሮች ተገዝተው ለትምህርትቤቶች መከፋፈላቸውን ገልጸዋል። “የተማሪዎች መቀመጫና ዴስኮች ግዥ፣ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና ዕድሳት፣ የትምህርት ቤቶች አጥር ጥገና እንዲሁም የጥናት ማዕከላት ግንባታና ጥገና ከተከናወኑ ተግባራት ይጠቀሳሉ” ብለዋል አቶ ተፈራ ፡፡ ከትምህርት ጥራት አንጻር እየገጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ኩረጃን ለማስቀረትና ኃላፊነት የሚሰማው የትምህርት አመራር ለመፍጠር ወላጆችን በትምህርት ስራ ለማሳተፍ፣ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የዳሞት ፑላሳ ወረዳ ትምህርትቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ጊቶሬ በበኩላቸው የትምህርት ዘመኑን ከመጀመራቸው በፊት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የንቅናቄ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን እቤት ውስጥ እንዳይቀር በዕድርና በሃይማኖት ተቋማት ጭምር ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፣ መደበኛ የትምህርት ሥራ ከመስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በሶዶ ከተማ አስተዳደር የሊጋባ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጌታቸው ዳና በበኩላቸው የትምህርት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ወላጆች፣ ተማሪዎችንና መምህራንን ያሳተፈ ንቅናቄ በዝግጅት ምዕራፍ መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ “በእዚህም የተማሪዎች መጻህፍት፣ መቀመጫዎችና የቤተ-ሙከራ ግብአቶች አስቀድመው እንዲሟሉ እና መማሪያ ክፍሎችና ግቢው ለትምህርት ሥራ ምቹ እንዲሆን ተደርጓል” ብለዋል፡፡ በመስከረም ወር የሚፈጠረውን የትምህርት መቀዛቀዝና የትምህርት ብክነት ለመከላከል ከነሀሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ መምህራን ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ወላጆችንና መምህራንን በማስተባበር የዘንድሮን የትምህርት ሥራ ውጤታማ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአብዮት ጮራ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ መምህራን ሕብረት ሰብሳቢ አቶ ማርቆስ ቱሬ ናቸው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን በጊዜ እንዲልኩ ከማድረግ ባለፈ የልጆቻቸውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የትምህርት ብክነትን፣ መጠነ-ማቋረጥና መቅረትን ለመቀነስ እንዲሰሩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። በእዚህ ረገድ ወላጆች ኃላፊነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ዕድር እና የሃይማኖት ተቋማትን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ማርቆስ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም