የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት የካይዘን የልህቀት ማዕከል ሊያስገነባ ነው

154

አዲስ አበባ  ኢዜአ መስከረም 19 / 2012 የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት በ 27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የካይዘን የልህቀት ማዕከል በአዲስ አበባ ሊያስገነባ ነው።

የካይዘን የልህቀት ማዕከሉ በጃፓን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን ከኢትዮጵያም አልፎ በአገልግሎቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን የሚያካትትም ነው ተብሏል።

በግንባታ ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የታደሙትም በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ፤ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መኮንን ያዬና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርሃኑ ፈይሳ ናቸው።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ጃፓን የካይዘን ፍልስፍናን ወደ ኢትዮጵያ ስታስገባ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ አልማ ነው።

የካይዘን ፍልስፍና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2011 ጀምሮ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ትብብርም ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የካይዘን አሰራር በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ እንዲሁም በአምራች ተቋማት ላይ ያለውን የምርት ብክነት ይቀንሳልም ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የካይዘን ፍልስፍናን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትንና የሃብት ብክነትን መቀነስ እንደቻለች ገልጸዋል።

ለዚህም ነው የጃፓን መንግስት ከኢትዮጵያም አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ የሚሆን የካይዘን የልህቀት ማዕከል በአዲስ አበባ እንዲገነባ 27 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በእርዳታ የሰጠው ብለዋል።

በቀጣይም የጃፓን መንግስት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ሁለንተናዊ የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጎልበት በትብብር እንሰራለንም ብለዋል አምባሳደሩ።

የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መኮንን ያዬ በኢትዮጵያ የሚገነባው የካይዘን የልህቀት ማዕከል የሁለቱን ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያጎለብታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውንም አሰራር በማዘመንና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

የልህቀት ማዕከሉ በኢንዱስትሪዎች አካባቢ ያለውን የስራ ባህል በማሳደግ፣ በጥራትና በአይነት የተሻለ ምርት ለማምረት ያግዛልም ብለዋል።

ሀገር በቀል እውቀትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልም ካይዘን አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መንግስት የጀመረውን መዋቅራዊ ለውጥንም ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርሃኑ ፈይሳ በበኩላቸው ካይዘን የሰራተኞችን የስራ ባህል ያሳድጋል፤ ምርታማነትን ይጨምራል ብለዋል።

ባለ አራት ፎቅና ከመሬት በታች አንድ ወለል ያለው ይኸው ግንባታ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ጥር 2021 ይጠናቀቃል፤ በተያዘለት ጥራትና ጊዜ እንዲከናወንም ክትትል ይደረጋል ተብሏል።

የጃፓኖቹ ፉጂታ ኮርፖሬሽን በግንባታ ስራው እንዲሁም ኒፖን ኮዬ በዲዛይንና ማማከር ስራ ይሳተፉበታል።