የመረጃ ነጻነት ቀን በመቀሌ ከተማ በፓናል ውይይት ተከበረ

76
መቀሌ (ኢዜአ) መስከረም 18 ቀን 2012 ዓ.ም ---ወቅታዊና ተአማኒ መረጃ ተደራሽ ማድረግ ለህዝቦች አንድነትና ትስስር የጎላ ሚና እንዳለው የትግራይ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። በዓለም ለ17ኛ ጊዜ በትግራይ ክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የመረጃ ነጻነት ቀን በመቀሌ ከተማ በፓናል ውይይት ዛሬ ተከብሯል። የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሊያ ካሳ በፓናል ውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ በህዝቦች መካከል ትስስርና አንድነት እንዲጠነክር ሚናው የጎላ ነው። ትክክለኛና ወቅታዊ  መረጃ የሌለው ማህበረሰብ  በሚናፈስ የሀሰት ወሬ የመጠለፍና የመጓዝ ዕድሉ የሰፋ መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል። ወይዘሮ ሊያ እንዳሉት ተአማኒ መረጃ ማሰራጨት በማህበረሰብ ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን በተለይ ወጣቱ ትውልድ በምክንያቲያዊነትና በመረጃ የተደገፈ ሞጋች ትውልድ እንዲሆን ያግዛል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙሀን ለህዝቦች አንድነትና ትስስር መጠናከር የሚያስችሉ መረጃዎችን ከመስጠት ይልቅ ልዩነትን የሚያጎሉ አቅጣጫ እየተከተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። "መረጃ ለልማትና ለማህበረሰብ እድገት" በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ በመድረኩ ላይ ያቀረቡት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሀዱሽ ካሱ ናቸው። ከትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ውጭ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ሊታሰብ እንደማይችል አመልክተዋል። "መረጃ ትልቅ ሀብት መሆኑን በማወቅ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል" ብለዋል። በክልሉ መረጃ በነጻነት ከመስጠት አንጻር የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ሀዱሽ "መረጃ መከልከል የህዝብን መረጃ የማግኘት መብት መገደብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል" ብለዋል። የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 አተገባበር ላይ ችግሮች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ በእንባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ገብረእግዚአብሔር ገብረሚካኤል ናቸው። በአዋጁ ላይ ማህበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብቱ የተቀመጡ ቢሆንም አተገባበሩ ብዙ እንደሚቀረው ነው የገለጹት። የውይይቱ ተሰታፊና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር በረከት ይሄይስ በበኩሉቸው  "በአዋጁ የተቀመጡ አንዳንድ አንቀጾች ህብረተሰቡ ትኩስ መረጃ እንዳያገኝ እንቅፋት የሆኑ ናቸው" ብለዋል። መረጃ ለማግኘት የ30 እና የ60 ቀናት የጊዜ ገደብ የሚሰጥ አዋጅ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት እንቅፋት በመሆኑ መከለስ እንዳለበት ጠቁመዋል። የፓናል ውይይቱን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋም ከመቀሌ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም