የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የመስቀል ደመራ ላይ በዓሉ ከሚፈቅዳቸው ስነ ስርዓቶች ውጪ የተለዩ እንቅሰቃሴዎች እንዳይደረጉ አሳሰበ

109
መስከረም 15/2012 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሚከበረው የመስቀል ደመራ ላይ በዓሉ ከሚፈቀዳቸው ስነ-ስርዓቶች ውጪ የተለዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ተግባሩን ለመፈጸም የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ። ኮሚሽኑ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግላጫ እንዳስታወቀው፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን የምታከብረው የመስቀል ደመራ ከኃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑም ባሻገር የአገርን መልካም ገጽታ በመገንባትና ቱሪስት በመሳብ ረገድ ጉልህ ሚና አለው። ይሁን እንጂ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተነሱ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ የግል አጀንዳቸውን ለማራመድ የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን እንደደረሰበት ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ በቤተ ክርስቲያኗ ለተነሳው ጥያቄዎች መንግስት ትኩረት መስጠቱን አብራርቷል። ለዚህም ከአስተባበሪዎች ጋር በመምከር ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረገው ጥረት አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱንም በአብነት ጠቅሷል። ሆኖም የቤተ-ክርስቲያንን ጥያቄ ሽፋን በማድረግ አንዳንድ አካላት ህዝበ ክርስቲያኑን ለማሳሳትና የእምነቱ ወግና ስርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ለማስኬድ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን እንደተደረሰበት የኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል። ኮሚሽኑ በመግለጫ እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የግል አጀንዳዎችን አንግበው የበዓሉን ስነ-ስርዓት ለማወክ የተዘጋጁ ሃይሎች መኖራቸው ተደርሶበታል። ስለሆነም ከበዓሉ ስነ-ስርዓት ውጪ፣ ግጭት ቀስቃሽና ብዝሃነትን የማይገልጹ፣ አንዱን የሚያሞግስ ሌላውን የሚያንቆሽሹ ፅሁፎች በማንኛውም መንገድ ይዞ መገኘት እንደማይቻልም አስገንዝቧል። በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ እና የተለዩ አርማዎችን በመያዝ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ስፍራ መምጣትም የተከለከለ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል። የደመራ በዓል ከሚፈቅዳቸው ስነ-ስርዓት ውጪ ሌሎች ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑንም የኮሚሽኑ መግለጫ አስታውሷል። ስለሆነም የሃይማኖት አባቶች፣ የየደብሩ አስተዳደሮች፣ የደመራ በዓሉን በኮሚቴነት የሚስተባብሩና የሚመሩት አካላት፣ ህዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም ወጣቶች ፖሊስ የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደረጉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። በሌላ በኩልም በአዲስ አበባና በተለያዩ አገሪቷ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዝግጅት የነበራቸው የአልሸባብና አይ ኤስ አይኤስ የሽብር ቡድኖች አባላት በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሽብር ቡድኖቹን እንዳስከፋቸው ጠቁሟል። አሁንም አፀፋዊ የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር አመቺውን ሁኔታ ሁሉ ለመጠቀም እንደሚፈልጉ መረጃዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሶ፤ ህብረተሰቡ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከት በአካባቢው ላሉ የፀጥታ አካላት መረጃ እንዲሰጥ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል። ኮሚሽኑ የመስቀል ደመራ በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ የሰላም የፍቅር የአንድነትና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም