በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አጠቃቃም ላይ ስርዓት በማበጀት የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት እንዲያመጣ ትኩረት ተሰጥቷል ተባለ

687

መስከረም 14/2012 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢንተርኔት አጠቃቀም በህግ አግባብ እንዲመራ በማድረግ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን እድል ለመጠቀም እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በአፍሪካ የኢንተርኔት አጠቃቀም ነጻነት ላይ ትኩረቱ አድርጎ የሚመክር አህጉር አቀፍ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ  ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ከ400 በላይ የዴጂታል ቴክኖሎጂ፣ የሰባዊ መብታና የህግ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የአፍሪካ የኢንተርኔት ነጻነት አሁን ያለበት ሁኔታ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ችግሮችና መፍትሄዎች እንዲሁም የአገሮች የዘርፉ ምርጥ ተሞክሮ በፎረሙ የሚዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ።

ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ሰበአዊ መብቶች እንዲጠበቁ ያካናወነችው ሪፎርም ጉባኤውን እንድታስተናግድ  እድል አንደፈጠረላት ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴሬክኖለጂ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ጀማል በከር በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ያለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ሁሉን አቀፍና አካታች እድገትን ማስመዝገብ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማስፋትና ዘርፉን የሚመለከት የህግ ማእቀፍ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

በተለይ ‘ወረዳ ትራንስፎርሜሽን’ በሚል ማእቀፍ ሁሉንም የአገሪቱ ወረዳዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስተሳሳር እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል።

የግብር አከፋፋልና ሌሎች የንግድ ትስስሮችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ቀልጣፋና ግልጽ የኢኮኖሚ ምህዳር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።

ግለሰብም ሆነ፤ የተለያዩ ቡድኖች ኢንተርኔት አገልግሎትን ሃላፊነት በጎደለው መልኩ እንዳይጠቀሙ የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አዋጅ የተረቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ አዋጁን ለማጸደቅ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ብለዋል።

አዋጁ ከኤሌክትሮኒክስ ግብይት በተጨማሪ አጠቃላይ የሳይበር ምህዳሩን እንዲቃኝ ተደርጎ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ የኢንተርኔት ነጻነት ፎረም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር ከ2014 ጀምሮ  በየዓመቱ እየተካሄደ ሲሆን፤ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ፎረሙን ከአንድ ዓመት በፊት ማስተናገዷ ይታወቃል።