የመስቀል በአል አከባበር በቤተ ጉራጌ

862
ሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ) የመስቀል በአል ሃይማኖታዊ በአል ቢሆንም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህሎቻቸውን እና እሴቶቻቸውን በማሳየት የሚያከብሩት በአል ነው። የመስቀል በአልን ከሌሎች በአላት ለየት የሚያደርገው ሰዎች በተለያዩ ንድፎች ያማሩ ባህላዊ ልብሶቻቸውን በመልበስ በጋራ ዳመራ በመደመር የሚያከብሩት በአል መሆኑ ነው። የበአሉ አከባበርም በርካታ የውጭ ሃገር ቱሪስቶችን ቀልብ የሳበና የዳመራው በአል በሚከበርበት ወቅት በርካቶቹ ወደ ሃገራችን በመምጣት ታዳሚ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የመስቀል ደመራ በአል በ2006 ዓም በዩኔስኮ በአለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ስለሆነም በአሉ ከሀገራችን አልፎ በሌሎች ልዩ ስፍራ እንዲሰጠው ምክንያት ሆኗል። በገጠራማው የሃገራችን ክፍል በወንዝ ሙላት ምክንያት ተለያይተው የከረሙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማገናኘቱ ረገድ የመስቀል በዓል የራሱ አዎንታዊ ሚና አለው። የመስቀል በአል በሁሉም አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በደቡቡ የሀገራችን ክፍል በተለየ ድምቀትና ባህላዊ ሁነት ይከበራል። በደቡብ የመስቀል በኣል ከሃይማኖታዊ ገፅታው በተጨማሪ በተለያዩ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ታጅቦ ይከበራል። የበኣሉ አከባበር እንደ የአካባቢው ይለያያል። በጉራጌ፣ በከንባታ እና በዶርዜ የመስቀል በአል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይከበራል። የመስቀል በአል በቤተ ጉራጌ ከወትሮው የተለየ ቦታ አለው። በስራ ምክንያት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት ብቻም ሳይሆን በጋራ እየበሉና እየጠጡ የሚያከብሩት በኣል ነው። በቤተ ጉራጌ የመስቀልን በአል ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም ጭምር ያከብሩታል። ለወትሮው ወደ ግጦሽ ሜዳ ወጥተው የዕለት ጉርሳቸውን ያገኙ የነበሩ የቀንድም ሆኑ የጋማ ከብቶች ታጭዶ በተዘጋጀላቸው መኖ ከቤት ሳይወጡ በአሉን እንዲያሳልፉ ይደረጋሉ። በቤተ ጉራጌ የመስቀል በኣል ለአንድ ቀን ብቻ ተከብሮ የሚያልፍ ቀን አይደለም። በብሄረሰቡ ተወዳጅ የሆነው የመስቀል በኣል በቀናት ተከፋፍሎ የሚከበር በኣል ነው። በቤተ ጉራጌ የመስቀል በአል ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ቀን ይከበራል። ከህፃናት ጀምሮ ወጣቶች እና አዛውንቱ የብሄረሰቡን ባህላዊ ምግብ ክትፎና ሌሎችን በመመገብ፣ በጭፈራና በፈንጠዝያ የመስቀልን በአል ያከብራሉ። የቀናቶቹን ስያሜና ባህላዊ ክዋኔዎቹን ቀጥለን እንመልከት። መስከረም 13 ቀን ወሬት የኸና ‘ወሬት የኸና’ ማለት በብሄረሰቡ ቋንቋ እንቅልፍ ከልካዩ ቀን የሚል ትርጓሜን የያዘ ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት የጉራጌ ሴቶች ለበአሉ ዝግጅት ለማድረግ የሚጓጉበት ቀን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ቀን ለበአሉ ለመመገቢያነት የሚያገለግሉ ባህላዊ ቁሳቁሶች ለአመት ከተሰቀሉበት ቦታ ወርደው በጥንቃቄ ተጣጥበው ዝግጁ ይሆናሉ።የፅዳት ተግባሩ ከአጥንት የተሰሩ ባህላዊ የመመገቢያ ማንኪያዎች፣ ከሸክላ የተሰሩ ጣባዎች እና ሌሎችንም ይጨምራል። ይኸው ቀን በሶዶ ክስታኔ ጉራጌዎች ‘የወልቀነ’ ወይም የሴቶች ቀን በመባል ይታወቃል። ቤቶች ከአፈር በተዘጋጁ ቀለማት ያሸበርቃሉ፤ አዳዲስ የኬሻ ጅባዎች ተነጥፎባቸው ለበኣሉ ዝግጁ ይሆናሉ። መስከረም 14 ቀን ደንጌሳት ይህ ቀን ልጆች እና ህፃናት ደመራ ደምረው ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን የሚያቀልጡበት ነው። ‘ደንጌሳት’ ወይም የልጆች ደመራ/እሳት የሚል ትርጓሜን የያዘ ሲሆን ልጆች ቀኑን በተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖች ለቀኑ ስላበቃቸው ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑታል። ከደመራው በኋላም ሴቶች የጎመን ክትፎ በማዘጋጀት በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውክልና በተዘጋጀ ጣባ በማድረግ ለምግብነት ያዘጋጃሉ። ባለትዳር የሆኑ የቤተ ጉራጌ አባላት በአንድ ጣባ የጎመን ክትፎው ተዘጋጅቶ ይሰጣቸዋል። ተምሳሌትነቱም የትዳር አጋሮች አንድ አካል አንድ አምሳል ናቸው ተብሎ ስለሚታመን የሚፈፀም ነው። መስከረም 15 ወኸመያ/ጨርቆስ/ በቤተ ጉራጌ ዋናው የመስቀል በኣል የሚከበርበት ቀን ነው ወኸመያ። ‘ወኸመያ’ ወይም አመት በአል የሚል ትርጉም አለው። በዚህ ቀን በሁሉም የብሄረሰቡ አካባቢዎች የእርድ ቀን ነው። በዕለቱም የሚታረደው በሬም ሆነ ወይፈን ሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ ስለ ሃገር ሰላም እንዲሁም ስለ በአሉ መልካሙን የመመኘት ምርቃት የሚወርድበት ነው። የቤተሰቡ አባላትም በእያንዳንዱ ምርቃት መጨረሻ ላይ ሶስት ጊዜ “ኬር ይሁን” በማለት ምርቃቱን ይቀበላሉ። ‘ኬር ይሁን’ ትርጉሙ ሰላም ይሁን እንደማለት ነው። በዚህ ባህላዊ የምርቃት ስነ ስርአት አብዛኛውን ጊዜ እንዲመርቁ የሚጋበዙት በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ አረጋውያን ሲሆኑ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እኩል ተሳትፎ ይኖራቸዋል። ከምርቃቱ በኋላም የቀረበውን ሰንጋ በማረድ ቁርጥ ስጋውን በተነጠረ ቅቤ በተዘጋጀ መበያ (ጨፉየ) እየነከሩ መመገብ የተለመደ ጉዳይ ነው። መስከረም 16 ያባንዳ እሳት/የጉርዝ እሳት/ ያባንዳ እሳት/የጉርዝ እሳት/ ማለት የአባቶች ደመራ ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ የሚያደርግበት የደመራ በአል ይከወናል። በዕለቱ አባቶች የተለየ ክብር ተሰጥቷቸው የደመራ በአሉን በምርቃት ያስጀምሩታል። ቀኑ ከባህላዊው ይልቅ መንፈሳዊ ይዘትን ተላብሶ ይከበራል። ጎረምሳና ልጃገረዶች ዳመራውን በመክበብ በተለያዩ ጭፈራዎች አካባቢውን ያደምቁታል። እገረ መንገዱንም ወጣቶቹ ለመተጫጨት የመጀመሪያ እይታ የሚያደርጉበትም ቀን ነው። ከጭፈራው በኋላም ሁሉም ወደ ቤቱ በመመለስ በራሱ ጣባ የተዘጋጀለትን ክትፎ ይበላል። በአንዳንድ የቤተ ጉራጌ አካባቢዎች ዕለቱ ‘የብርንዶ ቀን’ የክትፎ ቀን በመባል ይታወቃል። መስከረም 17 ንቅባር /የከሰል ማይ/ በዚህ ቀን ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ በአንድ አካባቢ የሚገኙ የቤተ ጉራጌ ነዋሪዎች ዳመራው ወደ ተቃጠለበት ቦታ በመሄድ የአካባቢያቸውን የዕድር ዳኛ በመቀየር አዲስ የሚመርጡበትና ቃለ መሃላ የማስፈፀም ተግባርን የሚያከናውኑበት ነው። ሁሉም የአካባቢው የቤተሰብ አባላት የተቃጠለውን የደመራ ከሰል እየዘለሉ በመጪው ዘመን መልካም ነገር እንዲገጥማቸው የሚመኙበት አልፎ ተርፎም የሚማፀኑበት ቀንም ነው። መስከረም 18 የፊቃቆ ማይ የአካባቢው ልጃገረዶች ለመጠቀሚያነት የሚውሉ ሰፌዶችን ለመስፋት የሚያገለግሉ ስንደዶዎችን የሚለቅሙበት ቀን ነው። የስንደዶ ለቀማው በባህላዊ ዜማዎች ታጅቦ ይከወናል። በቤተ ጉራጌ ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 23 የዘመድ መጠየቂያ ጊዜ ነው፤ የጀወጀ/የጀመቸ ተብሎም ይጠራል። ለአመት ተነፋፍቀው የቆዩ ቤተሰቦች ተገናኝተው ናፍቆታቸውን የሚገልፁበት ጊዜ ነው። የባል እንዲሁም የሚስት እናት እና አባት የሚጠየቁበት የተለያዩ ነገሮች በስጦታ የሚቀበሉበት ዕለት ነው። ሴት ልጆች ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ፣ ባርኔጣ፣ ጭራ እና ሌሎች ስጦታዎችን ሲያቀርቡ ባሎቻቸው ደግሞ የበግ ሙክት በመያዝ ይጠይቋቸዋል። ስጦታው የቀረበላቸው እናትና አባቶችም የልጆቻቸውን ባሎች እና ሚስቶች በየተራ ይመርቋቸዋል። ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ያለው ጊዜ በቤተ ጉራጌ ወጣቶች እጅግ ተወዳጅ ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች እና አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን ያሳያሉ፤ እግረ መንገዳቸውንም ለትዳር የምትሆናቸውን ጉብል መልከት መልከት ያደርጋሉ። የወጣቶቹ ባህላዊ ጨዋታ “አዳብና” በሚል ስያሜ የሚታወቅ ሲሆን እዚህም የተነፋፈቁ ወጣቶች ተገናኝተው በንግድና በተለያዩ ምክንያቶች ቆይተው ስለመጡባቸው ቦታዎች ይጨዋወታሉ። በአዳብና ጨዋታውም ወጣት ሴቶች ያላቸውን አዲስ ልብስ ለብሰው የሚወጡበትና የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ያማልላሉ። ፀጉራቸውን ሹሩባ ተሰርተው፣ ቅቤ ተቀብተው ከወትሮው በተለየ መልኩ አምረውና ተኩለው ወደ “አዳብና” የጭፈራው ቦታ ይመጣሉ። ወጣት ወንዶችም ቀልባቸው ያረፈባትን ሴት ለሚ በመስጠት ይመርጣሉ፤ ከዚያም ለሃገር ሽማግሌዎች በመንገር ወጉን እና ባህሉን ጠብቀው ለከርሞ የትዳር አጋራቸውን ያገኛሉ። በአዳብና ጭፈራ ወቅት ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ “የሙየቶች” የተለየ የጥበብ ትዕይንት ነው። በቤተ ጉራጌ የተመረጡ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ማንኛውም ሰው ‘ሙየት’ መሆን አይችልም። ሙየቶች የተለየ ቋንቋ እና አጨፋፈር ያላቸው የተረጡ ሰዎች ናቸው። ሙየቶች ለአዳብና ጨዋታው የተለየ ድባብን ያላብሱታል። የሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሚይዙት ልምጭም በአደይ አበባ የተሽቆጠቆጠ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የተለየ ነው። ሙየቶች በዕለቱ ከመግደል በቀር በምድር ያለ ሁሉንም ስልጣን ይሰጣቸዋል። በጨዋታው ላይ ያልተገባ እንቅስቃሴ የሚያደርግ እድምተኛ ካጋጠማቸው በያዙት ልምጭ እንካ ቅመስ የማለት መብታቸው በአዳብናው ህግ  የተረጋገጠ ነው። የተለየ ዜማቸውና ዳንሳቸው ሙየቶችን በአካባቢው ከሚታየው ቁጥር ስፍር ከሌለው ታዳሚ ለየት አድርጎ እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። ይህንን የመሰሉ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ የቱሪዝም መስህብ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል የቤተ ጉራጌ የመስቀል አከባበር በአል የሚነግረን ነገር የለም ትላላችሁ? አበቃሁ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም