ከ300 በላይ እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ ተወሰነ

789

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በእስር ላይ የነበሩ 304 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ወሰኑ።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ እንዳስታወቀው እሰረኞቹ ከሞት እስከ እድሜ ልክ የተፈረደባቸው ነበሩ።

ዛሬ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በይቅርታ የሚወጡት እስረኞቹ  ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ውግንና የሌላቸውና እስካሁን ድረስ መፈታታቸውን የማያውቁ እንደሆኑ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አመልክቷል።

በይቅርት እንዲፈቱ ከተወሰኑ መካከል 289ኙ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ናቸው።

ዘጠኙ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ ሲሆን፤ ሶስቱ ደግሞ የረጅም ጊዜ ፍርድ ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤቱ የቆዩ መሆናቸው ተመልክቷል።

ሌሎች ሶስት የኬንያ ዜግነት ያላቸው ናቸው።

እስረኞቹ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከዛሬ ጀምሮ ከሚወጡት እስርኞች መካከል የአካል ጉዳትና የጤና እክል ያለባቸው እንዳሉ ተጠቁማል።

በተመሳሳይ በክልል ያሉ እስረኞችም ከሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010  ጀምሮ እንደሚፈቱም ተጠቁሟል።

መንግስት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በ17 ቀናት ቆይታው በደረሰባቸው ውሳኔዎችና በአስቀመጠው አቅጣጫዎች መሰረት የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል።

በተለያዩ ምክንያቶች ተከሰው በእስር ላይ የነበሩ ታራሚዎችና በክስ ሂደት ላይ የቆዩ ክሳቸው ተቋርጦ መፈታታቸው ይታወሳል።