የሚዲያ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ስልጠና መስጠት የሚያስችል ተቋም ለማቋቋም መታቀዱ ተገለፀ

101
መስከረም 12/2012 የሚዲያ ኢንዱስትሪውና አገሪቱ የምትፈልገውን በትምህርት ተቋማት ተካተው የማይሰጡ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችል የስልጠና ተቋም ለማቋቋም መታቀዱ ተገለፀ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የጋዜጠኞች ደህንነትና ሌሎች በስልጠናና ትምህርት ውስጥ ተካተው እየተሰጡ ባልሆኑ ርዕሶች ማዕከሉ እንደሚሰራም አስታውቋል። ባለስልጣኑ ከአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ከአገሪቱ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከጅቡቲ፣ ኬኒያና ሱዳን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች በጋዜጠኝነት ደህንነትና ጥበቃ ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ነው። በዚሁ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት፤ እስካሁን ባለው ሂደት በትምህርት ቤቶች በሚሰጡ ትምህርቶችም ሆነ በስልጠና ላይ ስለጋዜጠኞች ደህንነት በትኩረት አልተሰራም። የሚዲያ ኢንዱስትሪውና አገሪቷ የሚፈልጉትን ክህሎት እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጋዜጠኝነት እየተሰጡ ያሉ ትምህርቶች ዙሪያ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በጥናት በመለየት ክፍተቱን ለመሙላት የሚያስችል የስልጠና ተቋም ለመመስረት እንደታሰበ ጠቁመዋል። ተቋሙን ለመመስረት ጥናቶች ተካሂደው መነሻ ሃሳብ ተዘጋጅቶ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ቀርቦ በጎ ምላሽ ከተገኘ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እውን እንደሚሆን አመልክተዋል። በዛሬው እለት የተጀመረው ስልጠና አገሪቱ የፕሬስ ነፃነት በማክበር በኩል በህጎችና ስምምነቶች ላይ የተደነገጉ ሃሳቦች በተግባር ለመቀየር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ጋዜጠኞች በሚሰሯቸው ዘገባ ያልተደሰቱ ሰዎች ከግድያ ጀምሮ የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸውና ይህ አይነት የውይይት መድረክ መፈጠሩ ጋዜጠኞች መብታቸውን እንዲገነዘቡ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ጋዜጠኞች መብታቸውን ለማስጠበቅና ለማስከበር የመደራጀት ጥቅም የጎላ መሆኑን ተናግረው፤  ባለስልጣኑ በሙያው ለተደራጁ ጋዜጠኞች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ተወከል በበኩላቸው አልጀዚራ በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ላሉ ባለሙያዎች ስልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረው፤ አሁን የሚሰጠው ስልጠና በኢትዮጵያ የተደረገው የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና በመሆኗ እንደሆነ ገልጸዋል። ስልጠናውን የሚሰጡት ሚስተር ዴቪድ ሪስ በተለያዩ አገሮች ለሚገኙ ዓለም ዓቀፍ እውቅና ላላቸው ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጋዜጠኞች ሥልጠና መስጠታቸውም ታውቋል። በተለያዩ ስፍራዎች በመጓዝ ዘገባዎችን የሚያጠናቅረውን ጋዜጠኛ ደህንነት አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀው፤ ደህንነቱን ለመጠበቅ ጋዜጠኛ ለዘገባ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ስለአካባቢው ሁኔታ በቅድሚያ ማጥናት እንደሚገባው ተናግረዋል። በተለይ የጦርነት ዘገባ ለመስራት ሲንቀሳቀስ ጋዜጠኛው ስለአካባቢው ሁኔታ በሚያጠናበት ጊዜ ጥቃት ቢደርስበት በምን መልኩ ህክምና እንደሚያገኝና በሄደበት አገር ስለሚገኝ የአገሩ ኤምባሲ መረጃ መያዝ እንዳለበት አስረድተዋል። ስልጠናው ጋዜጠኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አክብረው ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት ያላቸውን መብት እንዲገነዘቡና የጉዳት አዝማሚያ ሲገጥማቸው ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ የሚገነዘቡበት እንደሚሆን ታምኗል። እንዲሁም በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶችና በስራ ላይ በሚሰጡ ስልጠናዎች ላይ የጋዜጠኞች ደህንነትና ጥበቃ ላይ ትኩረት እየተሰጠ ባለመሆኑ የዛሬው ስልጠና ያልተለመደና ጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋልም ተብሏል። ከሌሎች አገሮች ጋዜጠኞች ጋርም ውይይት በማድረግ የልምድ ልውውጥ የሚገኝበትና የአገሪቱ ጋዜጠኞች ስራዎቻቸውን ከሌሎች አገሮች አንፃር እንዲፈትሹ እድል የሚፈጥር እንደሚሆንም ታስቧል። እ.አ.አ በ2018 ዘጠና አራት ጋዜጠኞች በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም