ኢትዮጵያና ዴንማርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መከሩ

81
መስከረም 12/2012 ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያና ዴንማርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችላቸው መንገዶች ላይ  ከዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር መቲ ፍሪደሪክሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከ74ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር መቲ ፍሪደሪክሰን ጋር የተገናኙ ሲሆን ውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ የትብብር መስኮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በተለይም በሃይል ግንባታ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያደርጉት ትብብሮችን አንስተው በቀጣይነት በሚከናወኑ ተግባራትም ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡ በውይይታቸውም በኒዮርክ ለአንድ ቀን የተካሄደውና ሁለቱ ሀገራት በጋራ ያዘጋጁት የሃይል ምንጭ ሽግግር ስብሰባ ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁ ለትብብራቸው ስኬታማነት አንድ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችልም መሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ዴንማርክ ለኢትዮጵያ በዋናነት በነፋስ ሃይል ግንባታዎች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በቅርቡ ለአሰላ የነፋስ ሀይል ግንባታ የሰጠችው የ200 ሚሊዮን እርዳታና ብድር ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም