የኢሬቻ የሰላም ሩጫ በወንዶች አትሌት በሪሁ አረጋዊና በሴቶች ደግሞ አትሌት ኦብሴ አብደታ አሸነፉ

286

መስከረም 11/2012 በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የኢሬቻ የሰላም ሩጫ በወንዶች አትሌት በሪሁ አረጋዊና በሴቶች ደግሞ አትሌት ኦብሴ አብደታ አሸናፊ ሆነዋል።

ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ታላቁ የኢሬቻ የሰላም ሩጫ ተካሂዷል።

በሩጫው ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ፣ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ አቶ ጀዋር መሐመድና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።

በዚህ ዝግጅት ላይ የጤና ሯጮችና አትሌቶች ተካፍለዋል።

በወንዶች አትሌቶች መካከል የተደረገውን ውድድር  በሪሁ አረጋዊ ከሱር ኮንስትራክሽን አንደኛ፣ ኃይለማርያም ኪሮስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ ደረጃን፤ ደጀኔ ደበላ ደግሞ ከውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ሶስተኛ በመውጣት አሸንፈዋል፡፡

በሴቶች ደግሞ ኦብሴ አብደታ ከለገ ጣፎ ለገ ዳዲ ከተማ  አንደኛ፣  መስተዋት ፍቅር በግል ሁለተኛ ስትወጣ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ አንቺዓለም ሃይማኖት ሶስተኛ በመሆን አሸንፈዋል፡፡

የወንዶች  ውድድሩን በቀዳሚነት ያጠናቀቀው አትሌት በሪሁ አረጋዊ በተወዳዳሪዎቹ በኩል ከባድ ፉክክር እንዳልገጠመው ተናግሯል።

በዚህ ውድድር ሲካፈል ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ መሆኑንም ገልጿል።

በውድድሩ የተካፈለችው ሌላኛዋ አትሌት ውድድሩ ደስ የሚል እንደነበር ገልጻለች። ነገር ግን “የጤና ሯጮች ከአትሌቶች ቀድመው በመለቀቃቸው እንደልብ መሮጥ አልቻልንም ነበር” ስትል ተናግራለች።

የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ቱጅባ በበኩላቸው የኢሬቻ የሰላም ሩጫ ባመረ መልኩ ተጠናቋል ብለዋል።

የውድድሩ አንዱ ክፍተት የነበረው የጤና ሯጮች ከአትሌቶች ቀድመው ሩጫ መጀመራቸው እንደነበር በማውሳት።

ይህም የሆነው በመድረክ መሪዎች ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ውድድር 50 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ቲሸርቶቹ በየዞኖቹና ወረዳዎቹ በመሸጣቸውና ቲ-ሸርቱን የገዙትም ተሟልተው ባለመምጣታቸው የተባለውን ያህል ቁጥር እንዳልተገኘ አቶ ነጋ ጨምረው ገልጸዋል።

በዚሁ ውድድር 1ኛ ለወጡት የዋንጫና የ50 ሺህ ብር፤ 2ኛ ለወጡት ደግሞ 30 ሺህ ብር፣ እንዲሁም ሶስተኛ ለወጡት ደግሞ የ20 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡