በኤሊደአር ወረዳ ህገወጥ የጦር መሳሪያን በቁጥጥር ሥር ላዋለ የፖሊስ አባል የማዕረግ እድገትና የገንዘብ ሽልማት ተሰጠው

179

አፋር መስከረም 11/2012   በአፋር ክልል ኤሊደአር ወረዳ በህገወጥ መንገድ ወደ መሀል ሀገር ሊገባ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ሥር ላዋለ የፖሊስ አባል የማእረግ እደገትና የገንዘብ ሽልማት ተበረከተለት።

የወረዳው ፖሊስ አባል የሆነው ሲራጅ አብደላ የዋና ሳጅነት ማዕረግና የ50 ሺህ ብር ሽልማት ከክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ እጅ ተቀብሏል ።

ዋና ሳጅን ሲራጅ አብደላ የማእረግና የገንዘብ ሽልማቱ የተበረከተለት መስከረም 6 ቀን 2012 አም ወደመሃል ሀገር ሊገባ የነበረ 29 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ በመያዙ ነው ።

ዋና ሳጅን ሲራጅ በወቅቱ መሳሪያው ወደ መሀል ሀገር እንዲያልፍ ከህገወጥ ነጋዴዎች ሊሰጠው የነበረውን 40 ሺህ ብር የመደለያ ገንዘብ አልቀበልም በማለት መሳሪያው እንዲያዝ አድርጓል ።

የአፋር ክልል ርእስ መስተዳደር አቶ አወል አርባ የማእረግ አድገቱን በሰጡበት ወቅት አንደተናገሩት የፖሊስ አባሉ የፈጸመው ተግባር የክልሉን ህዝብና መንግሰት ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ያኮራ ነው።

“ከግል ጥቅሙ ይልቅ ሀገር ወዳድነትና የህዝብ አገልጋይነት የሆነውን ፖሊሳዊ ተግባር በተጨባጭ አሳይቷል”ብለዋል ።

ዋና ሳጂን ሲራጅ አብደላ በበኩሉ የተሰጠው የማረግ እድገትና የገንዘብ ሽልማት ለእሱ ብቻ ሳይሆን ለሌችም ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የፖሊስ አባለት ማበረታቻ መሆኑን ገልጻል ።