ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለዘንድሮው ትምህርት ዝግጅት አጠናቋል

82
መስከረም 11/2012 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 30ሺ የሚጠጉ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በርቀት፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብር ትምህርት እንደሚሰጥ ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው ለሚያካሂደው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ስኬት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የተማሪዎች ህብረትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ለኢዜአ  እንደገለጹት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትምህርት የሚከታተሉት በዋናው ግቢና ሐረር ከተማ በሚገኘው የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ነው። በተቋሙ በመጀመርያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ ትምህርት ከሚከታተሉት መካከል 4ሺ 300 የሚጠጉት አዳዲስ ተማሪዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የተማሪ መኝታ፣መማሪያ፣ የቤተ መጽሃፍትና መመገቢያ ክፍሎች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይ ዘንድሮ ለሚጀመረው አዲሱ የትምህርት አሰጣጥ ፕሮግራም  ዩኒቨርሲቲው በካሪኩለም ቀረጻ ላይ መሳተፉን ጠቅሰው ለዚህም አስፈላጊው የመምህራን ቅጥር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በትምህርት ዘመኑ ተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማጠናከር  በመማር ማስተማሩ ስራና በተማሪ መምህር ግንኙነት ላይ መምህራኑ ማድረግ በሚገባቸው ነጥቦች ዙሪያ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችም ወደ ተቋሙ በሚመጡበት ወቅት ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተመሳሳይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ዘመኑ  በተለይ በድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራና ዘንድሮ አምስት በሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ እንዲሁም አንድ በመጀመርያ ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራም ለመክፈት ማቀዱን ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት አባል ተማሪ ፍሮምሳ ፍቃዱ  አዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደ ተቋሙ በሚገቡበት ወቅት እንግዳ እንዳይሆኑ ተማሪዎችን በአዲስ አበባና አዳማ ከተማ በመመደብ ወደ ስፍራው ሳይደናገጡ እንዲመጡ ይደረጋል ብሏል። እንዲሁም በደንገጎ፣ ሀረር፣ ድሬዳዋና ሀረማያ ከተማ የዩኒቨርሲቲውን መኪናና የተለያዩ ክበባት ተማሪዎችን በመመደብ ወደ ተቋሙ እንዲመጡ ለማድረግ  የዝግጅት ስራ ተጠናቋል፡፡ በተለይ ዘንድሮ በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲያከናውን ከተማሪዎችና ከአካባቢው ማህበረሰብ  ጋር ውይይት የማድረግ ስራ በጋራ እንደሚያከናውኑ ተናግሯል። የአካባቢው የአገር ሽማግሌ አቶ አቂል ኢብራሂም በበኩላቸው የመማር ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፤ የሁሉንም አካላት ርብርብ ይፈልጋል፤ በይበልጥ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶችን ጥረት እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡ ''በተቋሙ ባለፉት ዓመታት የመማር ማስተማር ስራ ላይ እንቅፋት ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን በጋራ እየፈታን ቆይተናል'' ያሉት አስተያየት ሰጪው ''ዘንድሮም ወደ ተቋሙ የሚመጡ ልጆችን በሰላም ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተቻለንን እንሰራለን'' ብለዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ62 ዓመት የመማር ማስተማር ስራ  ከ97 ሺ በላይ ተማሪዎችን በዲፕሎማ፣ በመጀመርያ፣ሁለተኛና ዶክትሬት ድግሪ አሰልጥኖ አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም