በክልሉ ተከስቶ በነበረ ግጭት የተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት ለማቋቋም ድጋፍ ይደረጋል- የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር

58
ሐዋሳ ኢዜአ መስከረም 10 ቀን 2012፡ በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ተከትሎ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስተያናት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን አጣርቶ ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። የቤተክርስትያኗ የዕምነት አባቶች ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና ዞን አመራሮች ጋር  ትላንት ተወያይተዋል ። ምክትል ርዕሰ መስተተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር  የደረሰውን  ጉዳት ለማስተካከል  ቤተክርስትያኗ ከመንግስት ጋር ተቀራርባ ለመስራት መፈለጓ ተገቢ ነው። በተለይም በሲዳማ ዞን የተፈጸሙ ችግሮችን በማጣራት አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል። "የወደሙ ቤተ ክርስትያናትን ለማቋቋም በጋራ እንሰራለን፤ በኛ በኩል የሚያስፈልጉ ድጋፎችን እናደርጋለን" ብለዋል። "ዞኑ የጀመረውን ስራ በማገዝ ግንባታዎች እንዲጠናቀቁና ያለ አግባብ ታስረዋል የተባሉትንም ጉዳይ በፍጥነት አይተን መፍትሄ እንሰጣለን” ሲሉም  ገልጸዋል። ክርክር የሌለባቸውና የይዞታ ማረጋገጫ ማስረጃ የሌላቸውን በማየት ማስረጃ እንዲያገኙ እንደሚደረግ የገለፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ ለመነጋገር ቢሯቸው ክፍት እንደሆነም አስታውቀዋል ። የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌንዳሞ በበኩላቸው በቅርቡ በዞኑ ተከስቶ በነበረው ግጭት  ስድስት አብያተ ክርስትያናት ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰዋል። "ህዝቡ የተጎዱ አብያተ ክርሰትያናትን ለመጠገን እየሰራ ነው "ያሉት ዋና አስተዳዳሪው  ከቤተ እምነቶቹ አባቶች ጋር በመነጋገር የተሻለ ነገር ለመስራት ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የማህበረ ቅዱሳን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ አለማየሁ  በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በቤተክርስትያኗ  አባቶችና ተከታዮች ላይ ጥቃቶች  እየደረሱ መሆኑን ተናግረዋል ። የመስቀልና ጥምቀተ  ባህር ይዞታዎችን የመቀማት፣ የማሰር፣ አምልኳቸውን በነጻነት እንዳይፈጸሙ የማድረግና የዕምነት ተቋማት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል ። በችግሮቹ ዙሪያ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ከዞን አመራሮች ጋር የተደረገው ውይይተና የተሰጠው ምላሽ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ገልጸዋል። ያሉትን ችግሮች በማጥናት ለመፍታት እንዲቻል ከቤተክርስትያኗና ከመንግስት አካላት የተውጣጣ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲዋቀር ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ሰይፉ ጠቁመዋል። በውይይት መድረኩ የሲዳማ፣ የከንባታ ጠንባሮ፣ የሀላባ፣ የስልጤና የሌሎች ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የሲዳማ፣ የጌዴኦ፣ የቡርጂና የአማሮ ሀገረስብከት ኃላፊዎችና የማህበረ ቅዱሳን ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም