ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባገዳዎችና አገር ሽማግሌዎች ጋር በኢሬቻ አከባበርና ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

179

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 10/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኢሬቻ በዓል አከባበርና ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ከአባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያዩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተደረገው ውይይት ላይ የኢሬቻ ባህል የኦሮሞ ባህል እሴትና መርህ በሆኑት አንድነት፣ ፍቅርና ይቅርታ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ በሰላማዊ መንገድ መከበር እንዳለበት ተገልጿል።

የምስጋና እና የእርቅ ቀን ተደርጎ የሚወሰደው የኢሬቻ በዓል በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል።

የመጀመሪያው የክረምት መውጣትን ተከትሎ ውሃ በሚገኝባቸው የተፈጥሮ አካባቢዎች፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወቅት በተራራማ ሥፍራዎች ይከበራል።

በውይይቱ ላይ አባገዳዎቹና የአገር ሽማግሌዎቹ በዓሉ በሰላማዊ መንገድና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚያከብሩት የደስታ በዓል እንዲሆን ባለድርሻ አካላት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይሚኒስትሩና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ነዋሪዎችን የሚመለከቱ የልማት፣ የሰላምና፣ ለውጡን የማስቀጠል ስራዎች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ከአባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በመናበብ እሴትን ቋንቋንና የኦሮሞ ህዝብ ባህልን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሰራም ተገልጿል።

ጠቅላይሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የኢሬቻ በዓል ዝግጅትና አከባበር ሰላማዊና ብሄራዊ አንድነታችንን ያንፀባረቀ እንዲሆን መግለፃቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።