"ያሆዴ መስቀላ " በሃዲያ

494
ማሙሽ ጋረደው /ሆሳዕና ኢዜአ/ ያሆዴ መስቀላ እንዲህ የክረምቱ ጨፍጋጋ የዝናብ ወራት ሲሸሹ፣መስኩ በልምላሜና በአደይ አበባ ሲያሸበርቅ በሃድያዎች ዘንድ ትልቅ ዝግጅት አለ። “ያሆዴ መስቀላ!” አዛውንቶች፣የሃገር ሽማግሌዎች ልጃገረዶች ወጣቶች ሁሉም በዓል የሚሆንበት ወቅት ነው። ያሆዴ መስቀላ በሀድያ ብሄር በርከት ካሉ እሴቶችና ወጎች እንዲሁም ክንዋኔዎች መካከል አንዱ ሲሆን ለማህበራዊ ክንዉኖች፡ለአንድነት፡መቻቻል፡ለዉጥ፡ ለአብሮነት ያለው ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ የሃዲያ ዞን የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት የመንግስት ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ባለቤት የሆኑት አቶ አድነዉ አሰፋ ይናገራሉ። “ያሆዴ “ማለት እንደ ብሄሩ የባህል ሽማግሌዎች ትርጓሜ መስቀል መጣ፡ገቢያዉ ደራ፡በይፋ ተበሰረ ብሎም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ሲሆን” መስቀላ” ማለት ደግሞ ብርሃን ፈነጠቀ በሚል ስያሜ እንደሚወሳም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ በወርሃ መስከረም አስራ ስድስት የሚከበር ሲሆን ወሩ ብርሃን፡ብሩህ ተስፋ፡ሰላም፡ፍቅር፡ረድኤት በረከት የሚሞላበት ተምሳሌት ወር ተደርጎ በብሄሩ ዘንድ እንደሚታመንና የጥንት የሀድያ አባቶችም በመስቀል አከባበር ላይ የነበራቸዉ አመለካከት ከፍተኛ በመሆኑ” ከባለቤቱ የከረመች ነፍስ በመስቀል አዉድ ትነግሳለች “የሚል ብሂል እንደነበራቸውም አቶ አድነው አስታውሰዋል።ወቅቱ እርድ የሚከናወንበት ቀን እንደ ዘመን መለወጫ የመጀመሪያ ቀን አድርገው በመውሰድ ማንኛውንም አይነት ክስተት ከዚያ ጋር አያይዘው ይቆጥሩት እንደነበር ተናግረዋል። በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሁሉም የቤተሰብ አባላት በዓሉን ለማድመቅ የየራሳቸዉ ድርሻ አላቸው። በብሄሩ አባቶች አብሮነታቸዉን ከሚያጠናክሩባቸዉ ማህበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ ቱታ/ሼማታ/ሲሆን ይህ ማለት የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደራጀ ቋሚ የሆነ ከአራት አስከ ስምንት አባላትን የያዘና በስጋ ቅርጫ የተደራጀ ማህበር ነዉ፡፡ የዚህ ማህበር አባላት ግንኙነት ያላቸዉ የሚተሳሰቡ የኢኮኖሚ አቅማቸውም ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን በመቀናጀት የበዓሉ እለት ከመድረሱ በፊት በጋራ ገንዘብ ማስቀመጥ ይጀምራሉ፤ በበዓሉ ወቅትም ለእርድ የሚሆን በሬ መግዣ ገንዘብ እንዳይቸገሩና በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ በማድረግ ረገድም ይሔ ህብረታቸው እንደሚረዳቸው ይናገራሉ። ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለከብቶች የግጦሽ ሳር የሚሆን ቦታ ከልሎ በማስቀመጥ የተቀመጠዉ የግጦሽ ሳር መሬት የበዓሉ ቀን ከብቶች ተለቀዉበት እንዲጠግቡ ልቅ የሚደረግ ሲሆን በአዲስ አመት መግቢያ እንኳን የሰዉ ልጅ እንሰሳትም ቢሆኑ መጥገብ እንዳለባቸዉ እንዲሁም የጥጋብ ዘመን እንዲሆን በብሄሩ በዓሉ ለሰዉ ብቻ ሳይሆን እንሰሳትም ሆዳቸዉ ሳይጎል አዲሱን አመት መቀበል እንዳለባቸው በመታመኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸውም አስረድተዋል። ለስጋ መብያ የሚሆን ቆጮ ብሎም ለአተካና የሚሆን ቡላ በማዘጋጀት ከጥቅምት እሰከ ጥር ባሉት ወራት ዉስጥ እንሰት በመፋቅ እናቶች በቡድን ተሰባስበው ዝግጅታቸዉን ማከናወን እንደሚጀምሩና በተጨማሪም ዊጆ|የቅቤ እቁብ| በመግባት ቅቤ በማጠራቀም ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ቅመማ ቅመሞችን በማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ልጃገረዶች በዓሉ እንዲያሸበርቅ ቤት መደልደል፡የተለያዩ ቀለማትን በመጠቀም የግርግዳ ቅርጻ ቅርጾችን በመስራት እንዲሁም ግቢ በማጽዳት የማሳመር ስራቸውን ያከናዉናሉ። ወጣት ወንዶች ለማገዶ የሚያገለግል በአባቶች ተለይቶ የተሰጣቸውን እንጨት ፈልጠዉ እንዲደርቅ በማድረግ እንዲሁም ጠምቦራ|ለደመራ የሚሆን ችቦ| በማዘጋጀት ግዴታቸውን የሚጠበቅባቸውን ያደርጋሉ። የቱታ አባላት ባስቀመጡት ገንዘብ ሰንጋ ለመግዛት መቻል ሜራ|የእብድ ገበያ|የሚያቀኑ ሲሆን የእብድ ገቢያ የተባለበት ምክንያት ከመስከረም 16 ቀደም ብሎ ያለው ቅዳሜ ሲሆን ገበያው ከወትሮው ለየት ያለና ግብይት የሚፈጸመው በጠዋት በመሆኑ ሁሉም ወደ ቤት ስራዉ ለመመለስ ጥድፊያ የበዛበትና እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ብቻ ግብይት የሚፈጸምበት በመሆኑ ነው። የቱታ አባላት ወደ መቻል ሜራ /የእብድ ገበያ/ በጠዋት በመሄድ ለበዓሉ የሚሆናቸውን ጥቁር ያልሆነ በአባላቱ ዓይን የገባ ሰንጋ ይገዛሉ በብሄሩ ለመሀላ ተደርጎ ስለሚቆጠር ጥቁር በሬ ለደስታ አይገዛም።መስከረም አስራ አምስት የበዓሉ ዋዜማ እለት ወጣቶች ያዘጋጁትን ጠምቦራ /የደመራ ችቦ/ የአካባቢዉን ነዋሪዎች በሚያዋስን ቦታ ላይ ይሰራሉ እናቶች ከቡላ፡ቅቤና ወተት የሚየዘጋጁት ጣፋጭ የሆነ እና ጣት የሚያስቆረጥመውን አተካና በማዘጋጀት የበዓሉን ዋዜማ ያደምቁታል። አመሻሽ ላይ ወጣቶች “ያሆዴ ያሆዴ “በማለት ይጨፍራሉ ይህ ክዋኔ እንደ ”ሆያ ሆዬ“ አይነት ሲሆን ለበዓሉ የሚሰጠዉን ቦታ በሚያሳይ መልኩ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያለዉ ነው። ወጣቶች በአካባቢዉ እየዞሩ በመጫወት ከአባቶች ምርቃት ይቀበላሉ፡፡ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ደመራዉ በተዘጋጀበት ቦታ ማምሻዉን ይሰባሰቡና አባቶች ደመራዉን የሚያቀጣጥሉበትን ችቦ በመያዝ ልጆችን በማስከተል አመቱ የብርሃን ፡የሰላም የአብሮነት፡የመተሳሰብ እንዲሆን ፈጣሪያቸዉን በመማጸን ደመራዉን ይለኩሳሉ። ወጣቶች በተለመደዉ መልኩ ያሆዴ ያሆዴ በማለት እንዲጫወቱ ቦታዉን በማስረከብ ክብ ሰርተዉ ለዚህ አመት ያደረሳቸዉን አምላክ በማመስገን አዲሱ አመት ሰላም እንዲሆን በመማጸን ደመራዉ ተቀጣጥሎ እንዳለቀ በእድሜ ተለቅ ከሚሉት አባወራ ቤት ሰብሰብ ብለዉ ደስታቸዉን ያስቀጥላሉ። የእርድ ስነ ስርዓቱ መስከረም አስራ ስድስት የሚደረግ ሲሆን የቱታ/የቅርጫ/ ማህበሩ እርድ የሚከናወነዉ በየአመቱ በአባላቱ ቤት በዙር ነው። የእርድ ስርዓቱ በሚከናወንበት ቤት ደጃፍ አባላቱ ቤተሰቦቻቸዉን በመያዝ በአንድነት በመሰባሰብ እርዱ ከመከናወኑ በፊት /የጋቢማ/ ስርዓት ይከናወናል። ይህም እድሜ ጠገብ ሽማግሌዎች ቅቤ እና ወተት በሚታረደዉ በሬ ላይ እያፈሰሱ” ለምለም ሳር "በመያዝ በሬዉን እያሻሹ አዲሱ አመት ለህዝብ እና መንግስት የሰላም አመት እንዲሆን ልጆች ለወግ ለማዕረግ የሚበቁበት መሀኖች የሚወልዱበት የተዘራው ዘር ለፍሬ ፈጣሪያቸውን የሚማጸኑበት ነው። ከዚህ በኋላ እርዱ ይከናወንና ከበሬዉ ሻኛ በቀር ስጋዉ ሙሉ በሙሉ በአባላቱን ቁጥር መሰረት በማድረግ የሚከፋፈል ይከፋፈላል። ከተመደበው ስጋ ተወስዶም እርዱ የተፈጸመበት ቤት ተሰጥቶ ክትፎ ይዘጋጅና ለሙሉ የቤተሰብ አባላቱ ቆጮ፡ ቅቤ በበቂ ሁኔታ ተደርጎ አስፈላጊዉ ነገር ሁሉ ቀርቦ እንደገና ለአመቱ እንዲያደርሳቸዉ ተመራርቀዉ በደስታ መመገብ ይጀመራል። የበሬው ሻኛ በተረኛው ቤት ተቀምጦ በ3ኛው ቀን የቱታው አባላትና የአካባቢ ሰዎች ተጠርተው በአባቶች ምርቃት ተደርጎ በአንድነት ሆነው ምክክር በማድረግ ለቀጣይ አመት የሚሆን እቅድ በማዘጋጀት ተጨዋውተው የሚለያዩበት ነው።በየቤቱ የሄደዉ ቅርጫ በፍጹም ለብቻ አይበላም አቅመ ደካሞችን በማብላት ብሎም መረዳዳት ዋነኛው ዓላማው ሲሆን በዓሉ በሚከበርበት ሰሞን የሩቅ እና የቅርብ ቤተሰብ ይሰባሰባል። እንዲሁም ተጣልቶ የከረመ ሰው እርቀ ሰላም በማውረድ አዲሱን አመት በንጹህ ህሊና ይዋሃዳል። የሃዲያዎችን ያሆዴ መስቀላ ጨምሮ በደቡብ ክልልና በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች ከሚከበሩት ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ጋር ተያይዞ ተጠናክሮ የቀጠለው የህዝቦች አብሮነት ከፍተኛ ማህበራዊና ስነልቦናዊ አንድነትን የሚፈጥር ነው። ህዝብን አንድ በማድረግ ለመመካከር ያለፈውን ችግር ለመፈተሽ ወደፊት የሚሆነውንም ለመለየት እያገለገሉ ያሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ይበልጥ ተጠናክረው ትውልድን ለማነጽ እንዲውሉ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም