በዞኖቹ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ142ሺህ የሚበልጡ ሕፃናት ለመማር ተመዝገቡ

104

ነቀምቴ መስከረም 10/2012 ፡- በምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ ዞኖች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ142ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ሕፃናት ለመማር መመዝገባቸውን የየዞኖቹ የትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ ፡፡

ከተመዘገቡት መካከል 73ሺህ 278 ሕፃናት በምዕራብ ወለጋ ዞን የሚገኙ ናቸው።

የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ኃይሉ እንዳሉት ህጻናቱ ለቅድመ መደበኛና ለመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም የተመዘገቡ ናቸው።

ህጸናቱ  በተያዘው የትምህርት ዘመን በዞኑ 20 ወረዳዎችና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመማር ተዘጋጅተዋል።

ከተመዝጋቢዎቹ መካከል 34ሺህ 524 ሴቶች ይገኙበታል።

በዞኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርትና የአስተዳዳር አካላት ፣7የትምህርት ቤት ኮሚቴ አባላት ፣ከተማሪ ወላጆችና መምህራን ጋር በመወያየት ለግባራዊነቱ መዘጋጀታቸውን ኃላፊው አስረድተዋል ፡፡

በግምቢ ከተማ የመድኃኔዓለም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ምሬሣ ጉዲና በሰጡት አስተያየት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር የዘመኑን የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማሳካት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

መምህራን ቀደም ብለው በትምህርት ቤታቸው በመገኘት የትምህርት ዕቅዳቸውን በማዘጋጀት የተማሪዎች ምዝገባ ማካሄዳቸውን አመልክተዋል።

በዘመኑ ተማሪዎች የትምህርት ቤቱን ሕግና ደንብ ጠብቀው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከተማሪ ወላጆች ጋር በቅርበት ለመሥራት እንደተዘጋጁ የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ኃይሌ ወርቅነህ ናቸው።

የግምቢ መሰናዶ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አበራ የማነ በበኩላቸው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር ከትምህርት ባለሙያዎች፣ ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የዞኑ ህብረተሰብ ለተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ስራና ለትምህርት ቤቶች የውስጥ ድርጅት ማጠናከሪያ እንዲረዳ በጥሬ ገንዘብ ፣ በቁሳቁስና በጉልበት ከ41 ሚሊዮን በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማድረጉም ተመልክቷል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ለ3ሺህ 121 የችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ከ1 ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የትምህርት ቁሣቁሶች ድጋፍ መደረጉም ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በምሥራቅ ወለጋ ዞን 68ሺህ776 ሕፃናት ለቅድመ መደበኛና ለመደበኛ ትምህርት መመዝገባቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ገልጿል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ያደታ ኢታና እንዳሉት ከተመዘገቡት መካከል 17ሺህ511 ለቅድመ መደበኛ ቀሪዎቹ ደግሞ አንደኛ ክፍል ገብተው የሚማሩ ናቸው።

በምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ  1ሺህ 684 አንደኛ፣ ሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከ963ሺህበላይ ተማሪዎች የዘመኑን ትምህርት እንደሚከታተሉ ይጠበቃል።