በቡሬ ወረዳ አደንዛዥ እፅ ሲያለሙ የተገኙ ግለሰቦች ተያዙ

93
መቱ ኢዜአ መስከረም 10 ቀን 2012 በኢሉአባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ በድብቅ በማሳቸው ላይ አደንዛዥ ዕፅ ሲያለሙ ተገኝተዋል ያላቸውን ሶስት ግለሰቦች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ። የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ታረቀኝ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በወረዳው ዕድገት ፋና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሶስት ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው ጓሮ አደንዛዥ ዕፅ ሲያለሙ ተደርሶባቸዋል። ግለሰቦቹ የመኖሪያ ቤታቸውን ጓሮ በአጥር በመከለል ዕፅ እያለሙ እንደሆነ ፖሊስ ከህብረተሰቡ  በደረሰ ጥቆማ መሰረት ተከታተሎ ሊይዛቸው እንደቻለ ተናግረዋል ። በተጨማሪ ተሳታፊ ነበር የተባለ  ሌላ  አንድ ግለሰብ ለጊዜው በመሰወሩ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል። ለጊዜው የተሰወረው ግለሰብ ለስራ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲዘዋወር ከሌላ አካባቢ ያመጣውን እፅ የሰጣቸውን መሆኑን የተያዙት ሰዎች በሰጡት ቃል መግለጻቸውን  ኮማንደሩ አመልክተዋል። እንደ ኮማንደር ታረቀኝ ገለጻ ግለሰቦቹ ተይዘው  ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፤ በማሳቸው ላይ የነበረው ዕፁ ተነቅሎ እንዲወገድ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም