የባህርዳር ሞጣ ደጀን መንገድ መገንባት የዘመናት ጥያቄያቸውን ምላሽ የሰጠ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ

94
መስከረም 10/2012 ከባህርዳር -ሞጣ ደጀን የሚወስደው የአስፓልት መንገድ መገንባት የዘመናት ጥያቄያቸውን ምላሽ የሰጠና ሰርተው ለመለወጥም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። የባህርዳር- ዘማ ወንዝ -ፈለገ ብርሃን 175 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ በቅርቡ መመረቁ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ኢዜአ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል በደብረወርቅ ከተማ በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩት አቶ መኩሪያው ይበይን በሰጡት አስተያየት የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ የአካባቢው እድገት ውስን ሆኖ እንዲቆይ ማድረጉን ገልጸዋል። ቀደም ሲል በተሰማሩበት የሆቴል የአገልግሎት ዘርፍም ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ግን አገር አቋርጭ ተሽከርካሪዎች እየገቡ  ማረፊያ በመሆኑ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል። የመንገዱ መገንባትም የገበያ እንቅስቃሴው መነቃቃት ከማሳየቱም በላይ ለወጣቶች የስራ እድል ለማመቻቸትና ለአካባቢው እድገት መፋጠን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል። "የመንገዱ መገንባት በአካበቢው የሚመረተውን የጥራጥሬ ምርት ወደ ማሃል ሃገር  ገበያ ለማቅረብ አስችሎናል "ያሉት ደግሞ በጥራጥሬ ንግድ የተሰማሩት አቶ መለሰ ስሜነህ ናቸው። ቀደም ሲልም ከአካባቢ ገበያ የሚገዙትን የጥራጥሬ ምርት ወደ ማሃል ሀገር ገበያ ለማቅረብ በ የትራንስፖርት እጥረት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል። መንገዱ ተሰርቶ ለአገልገሎት መብቃቱ   ጊዜ፣ ጉልበትንና ወጪን በመቆጠብ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ ማካሄድ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። የአካባቢው ነዋሪ ወጣት መሰረት ሳህሉ በበኩሉ " የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች ዕድገታቸው እንዲፋጠንና ስራ አጥ ወጣቶችም  የስራ ዕድል አግኝተን ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል "ብሏል። የሃገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ አሽከርካሪ አቶ አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው የመንገዱ መሰራት ወደ አዲስ አባባ የሚደረገውን ጉዞ እንዳሳጠረው ተናግረዋል። በተገነባው መንገድም የትራፊክ ምልክቶች እንዲተከሉና አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የመንገድ ጥራት ችግር እንዲስተካከልም አሳስበዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት የአስፓልት መንገድ መገንባት የዘመናት ጥያቄያቸውን ምላሽ  ከመስጠቱም በላይ የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን የሚያግዝና  ሰርተው ለመለወጥም ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው። "የሁሉም ልማቶች የጀርባ አጥንት የሆነው መንገድ ነው " ያሉት ደግሞ በመንገዱ ምረቃ ወቅት የነበሩት   ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። እሳቸው እንዳሉት  የመንገዱ መገንባት በአንድ በኩል ከባህርዳር -ሞጣ -አዲስ አበባ፣ ሌላው  ከሞጣ ጃራገዶ -ወደ ደቡብ ጎንደር የሚያሻግረው መንገድ በማስተሳሰርና የትራፊክ ፍሰቱን እንዲሳለጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። እንዲሁም በዚህ ዓመት ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ከደብረ ማርቆስ ስናን-ድጎጽዮን -ሞጣ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ለአካባቢው  ዕድገት መፋጠን ጉልህ ድርሻ  እንደሚኖረውም ጠቁመዋል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው መንግስት ለመንገድ መሰረተ ልማት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በየዓመቱ በመመደብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተያዝነው ዓመት አዳዲስ መንገዶችን ከማስጀመር በዘለለ  ያልተጠናቀቁም በፍጥነትና በጥራት ከፍጻሜ እንዲደርሱ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙም  አመልከተዋል። እንደሚኒስትሯ ገለጻ በተለይም ሰው ሁሉ ሲጓጓለት የቆየው ከባህርዳር- ዘማ ወንዝ -ፈለገ ብርሃን የ175 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ትርፍ አምራች በሆነው አካባቢ ተገንብቶ መጠናቀቅ ለአካባቢው ዕድገት መፋጠን ድርሻው ከፍተኛ ነው። "የዚህ መንገድ መገንባትም የገጠርና የከተማ ህዝብን ከማገናኘት ባለፈ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርት ግብዓቶችን በፍጥነት እንዲሰራጩ የላቀ ድርሻ አለው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም