በደቡብ ክልል የተሸከርካሪ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን በልዩ ሁኔታ ዛሬ ተጀመረ

61
ሀዋሳ መስከረም  09/2012፡- በደቡብ ክልል የተሸከርካሪ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋንን ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 30 የሚቆይ በልዩ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተገለጸ። ይህም ህግን የማስከበር ዘመቻ መሆኑን የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጠት መግለጫ አስታውቀዋል ፡፡ በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና ኢንፎርሜሽን ብቃት ዳይሬክተርአቶ መርከቡ ታደሰ እንዳሉት ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 30 በዘመቻ የሚሳተፉ በየደረጃው ላሉ አስፈፃሚ አካላት እንዲዘጋጁ ተደርጓል። “በተለይ በስፋት ወረዳዎች ላይ የሚንቀሳቀሱት ባለሶስትና ባለሁለት እግር ሞተር ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን ለመግዛት እንዳይቸገሩ ኩባንያዎቹ ባለሙያዎቻቸውን ወደስፍራው በመላክ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉም ይደረጋል” ብለዋል። የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ረዳት ኮሚሽነር ታዬ ጫርጋ በበኩላቸው ተሸከርካሪዎች ያለሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሚደነግገው አዋጅ ከ2005ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን አስታውሰዋል። ሆኖም በባለድርሻ አካላት ክፍተቶች የተነሳ በሚፈለገው ልክ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል ፡፡ በሚካሄደው ዘመቻ ህጉን ተላልፎ የተገኘ ግለሰብ በህግ እንደሚጠየቅ አመልክተው የህግ አስፈፃሚ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር የመድኅን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የዕቅድና መረጃ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ መሠረት ገብረኪዳን እንደገለጹት በሀገር ደረጃ ዝቅተኛ የነበረውን የሶስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ለማሳደግ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ሰፊ ንቅናቄ ተካሂዷል ፡፡ በንቅናቄው ከፌዴራል እስከ ዞንና ልዩ ወረዳዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ተፈጥሮ የተሻለ ስራ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል። በተለያዩ ከተሞች የአደባባይ የንቅናቄ መድረኮች ተካሂደዋል፤ ከባለንብረቶች አደረጃጀቶች ጋርም እንዲሁ፡፡ በዚህም 207 ሺህ 197 ተሸከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን መድን ሽፋን ማደስና መግዛት መቻላቸውን ያመለከቱት አቶ መሠረት ይህም ሀገራዊ ሽፋኑን ከ64 በመቶ ወደ 88 በመቶ ማድረሱን አስታውቀዋል ፡፡ በቀጣይም ሙሉ በሙሉ ለማድረስ በሀገር ደረጃ ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ በልዩ ሁኔታ ህግን የማስከበር ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል። በተሸከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚደርሱ አደጋዎች እጅግ እየበዙ እና ጉዳታቸውም እየከፋ ይገኛል፤ ተጎጂዎች ይህን ችግር በተወሰነ መልኩ እንዲቋቋሙ እና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እዲያገኙ ለማስቻል የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ መሆኑ እንደሚበጅ ተመልክቷል      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም