ሶስተኛውን ዙር የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ለማስፈፀም 30 ሚሊዮን ዶላር ተመደበ

110
መስከረም 9/2012 በኢትዮጵያ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማዳረስ እየተተገበረ ላለው የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ 30 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተገለፀ። ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚውለውና የዓለም ባንክ የሚስተዳድረው ገንዘብ የተገኘዉ ከአዉሮፓ ህብረት፤  ከኦስትሪያ  ዲቨሎመንት ኤጀንሲ፣ ከአይሪሽ ኤይድ፣ ከሲዊዲን ኢምባሲና ሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት ነው። የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍትሃዊና ተደራሽ እንዲሆኑና ባለተማከለ ደረጃ የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን ለማድረግ የሚሰራ ፕሮግራም ነው። የትኩረት አቅጣጫዎቹም ጤና፣ ትምህርት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የአካባቢ ንፅህና፣ የገጠር መንገድና ግብርና የልማት ዘርፎች ናቸው። የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሶስተኛዉ ዙር ትግበራን በተመለከተ ዛሬ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይም ከወረዳና ከክልል የተጋበዙ የሚመለከታቸው አካላትን ጨምሮ የዓለም ባንክ ተወካዮችና የእርዳታ ሰጪ አካላት  ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ላለፉት ዓመታት በሁለት ዙር የተተገበረ ሲሆን ዘንድሮ ሶስተኛውን ዙር ወደስራ ለመግባት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ በይፋ መጀመሩን የፕሮግራሙ የአቅም ማጎልበት ባለሙያ ወይዘሮ መስከረም ግርማ ተናግረዋል። ፕሮግራሙ ከዚህ በፊት በ223 ወረዳዎች የተተገበረ ሲሆን ዘንድሮ በሚተገበረው ሶስተኛዉ ዙርም ተደራሽነቱን በማስፋት ወደ 300  ወረዳዎች ያድጋል ብለዋል።  በመጪዎቹ ዓመታት የወረዳዎቹ ቁጥር ወደ 500 ያድጋል ተብሏል። ወይዘሮ መስከረም አክለውም ተፈጥሮዊና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎ በሚከሰቱበት ወቅት  የሚመለከተዉ አካል ችግሩን ተረድቶ ፈጣን ምላሽ  እንዲሰጥ የማስተባበር ስራም በፕሮግራሙ አማካኝነት ይከናወናል ሲሉም ተናግረዋል። ከወረዳና ከክልል የመጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደገለፁት ከዚህ በፊት ለሚያቀርቡዋቸው የማህበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ የማይሰጣቸው በመሆኑ ለችግር ይዳረጉ ነበር። የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ  ግን መሰረተ ልማትን ጨምሮ አጠቃላይ የማህበራዊ አገልግሎት ችግር ሲያጋጥማቸው ለሚያቀርቡት ጥያቄ የተሻለ ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይህን ዓይነት አገልግሎትየማያገኙ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ተሳታፊዎቹ በፕሮግራሙ አማካኝነት የሚካሄደው ተግባር መስፋፋት እንዳለበት አሳስበዋል። ህብረተሰቡም የሚቀርቡለትን ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች በተገቢዉ መንገድ መጠቀምና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባቸዉ ምክረ ሃሰብ ሰተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም