ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዲሱን ፍኖተ ካርታ ለመተግበር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያጠናቀቁ ነው

94

መስከረም 9/2012 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተያዘው ዓመት አዲሱን ፍኖተ ካርታ ለመተግበር የሚያስችላቸውን ዝግጅት በአብዛኛው ማጠናቀቃቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዘንድሮው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ምደባ እስከ መስከረም 19 ቀን 2012 ዓም ይጠናቀቃል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ለመጪዎቹ አስር ዓመታት የሚተገበር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ  ተዘጋጅቷል።

ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ፍኖተ ካርታው ከተመለከታቸው የዘርፉ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የከፍተኛ ትምህርትን ጥራትና ብቃት ማሳደግ አንዱ ነው።

በዚህም መሰረት የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ጉድለቶች የሚሞሉ የጋራ የትምህርት ዘርፎች (ኮርሶች) በፍኖተ ካርታው ተለይተዋል።

በተያዘው ዓመትም ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመደቡ አዲስ ተማሪዎች እነዚህን የትምህርት ዓይነቶች እንዲወስዱ የሚያስችለው ዝግጅት መጠናቀቁን ነው ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የተናገሩት።

ሚኒስትሯ እንዳሉት በመጀመሪያ ዓመት ለሚሰጡት የጋራ የትምህርት ዓይነቶች የሚያስፈልገው የመምህራን ቅጥርና የመማሪያ መፅሃፍትና ሞጁሎች ዝግጅት 95 በመቶ ሥራ ተጠናቋል።

በቅርቡም እየተካሄደ ያለውን ዝግጅት በአካል የሚገመግም ቡድን በየዩኒቨርስቲዎቹ ይሰማራ ብለዋል።

ከዘንድሮው የትምህርት ዘመን አንስቶ የዩኒቨርስቲዎች የመጀመሪያ ዲግሪ  ትምህርት ዝቅተኛ የቆይታ ጊዜ አራት ዓመት ይሆናል።

በተከለሰው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት መሠረትም በመጀመሪያ ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ የተማሪዎች ቅበላ የሚካሄደው በአራት የትምህርት ዘርፎች ይሆናል ተብሏል፡፡

እነዚህም የተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ የመምህርነት፣ በማህበራዊ ሳይንስ እና በማሕበራዊ ሳይንስ መምህርነት ዘርፎች ናቸው።

በሁለተኛው መንፈቅ ደግሞ የተማሪዎችን የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤት መሠረት በማድረግ  በህግ፣ በህክምና፣ በእንስሳት ህክምና፣ በፋርማሲ እና በኢንጂነሪንግ ዘርፎች ምደባ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

የሌሎቹ የሙያ መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ የተማሪዎችን ዓመታዊ ውጤት መሠረት በማድረግ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ ያስታወቁት።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲዎችን በተዕኮና በልሕቀት የመለየቱ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ይህም ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሂደት የሚተገበር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዘንድሮ በመንግስት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚመደቡት 142 ሺህ 943 ሰልጣኞች መካከል 43 ከመቶው ሴቶች ናቸው።

አዲስ ተማሪዎችን በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመመደቡ ተግባርም እስከ መስከረም 19 ቀን 2012 ዓም ድረስ እንደሚጠናቀቅም ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ገልፀዋል።