የአዲስ አበባና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ለሚቀበሏቸው ተማሪዎች የቅድመ መግቢያ ፈተና መስጠት ጀመሩ

84

አዲስ አበባ  መስከረም 9/2012  የአዲስ አበባና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በ2012 ዓ.ም ለሚቀበሏቸው አዲስ ተማሪዎች የቅድመ መግቢያ ፈተና ዛሬ መስጠት ጀመሩ።

የአዲስ አበባ እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠልና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሀይል ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት አድርገው የተቋቋሙ ናቸው።

በዚህም በአፕላይድ ሳይንስ፣ በምህንድስናና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስኮች ብቁና በአለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትምህርት እየሰጡ ይገኛሉ።

ዩኒቨርስቲዎቹ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ በየአመቱ በሚሰጠው አገር አቀፍ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡትን ይቀበላሉ።

ሆኖም ተማሪዎቹ ወደትምህርት ተቋማቱ ለመግባት በተቋማቱ የሚሰጣቸውን የቅድመ መግቢያ ፈተናን በተጨማሪ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

የከፍተኛ ትምህርቱን በእነዚህ ዩኒቨርስቲዎች መቀጠል የሚፈልግ ማንኛውም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን የወሰደና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ በቅድመ መግቢያ ፈተናው መሳተፍ ይችላል።

በዚህም መሰረት ዩኒቨርስቲዎቹ ዘንድሮ ለሚቀበሏቸው አዲስ ተማሪዎች ያዘጋጀውን የቅድመ መግቢያ ፈተና ዛሬ መስጠት ጀምረዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በተለይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቁ፣ ተፈላጊና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ማፍራት ይቻል ዘንድ ብቃታቸው የተረጋገጡ ተማሪዎችን በመለየት ነው የሚቀበለው።

ዩኒቨርስቲው ዘንድሮ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች ብቃት ለመለየት የሚያስችለውን ፈተና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የመግቢያ ፈተናው እየተሰጠ ያለው አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በሚገኙ 40 ማዕከላት መሆኑንም አመልክተዋል።

የቅድመ መግቢያ ፈተናው ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ሂሳብና ኢንግሊዝኛ የትምህርት ዓይነቶችን አካትቷል።

ዘንድሮ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ 3 ሺህ ተማሪዎችን የሚቀበሉ እንደሆነ ተገልጿል።

የአዲስ አበባና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የአገሪቱ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከልና ሞዴል የምርምር ተቋም ለመሆንም እየሰሩ የሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው።