የጋህአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የቀጣይ ስራዎችን አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቀቀ

199

መስከረም 9/2012   የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ /ጋህአዴን/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በጋምቤላ ከተማ ሲያካሄድ የቆየውን መደበኛ ስብሰባ የቀጣይ ስራዎችን አቅጣጫ በማስቀመጥ አጠናቀቀ።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ ትናንት የተጠናቀቀውን  ስብስባ አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ኮሚቴው ባለፈው ዓመትና በቀጣይ እቅዶች ዙሪያ በስፋት በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፋል።

ወይዘሮ ባንቻየሁ ድርጀቱ በ2011 በጀት ዓመት አልፎ- አልፎ ከነበሩት የጸጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ በተሻገሩ የልማትና የፖለቲካ ስራዎች ላይ በስፋት መወያየቱን ተናግረዋል።

በተለይም በትምህርት፣ መንገድ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የታቀዱት የልማት ስራዎች በተፈለገው ደረጃ አለመከወናቸውን ኮሚቴው ገምግሟል።

” በ2012 በጀት ዓመት ካለፈው ዘመን በተሻገሩ የልማትና የፖለቲካ ስራዎች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል “ብለዋል።

ኮሚቴው በ2012 በጀት ዓመት በተለይም የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ ህገ- ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመግታንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ውሳኔ አሳልፏል።

ወይዘሮ ባንቻየሁ እንዳመለከቱት በክልሉ ውስጥና በጠረፍ አካባቢ የሚካሄዱ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መግታት በሚቻልባት ዙሪያ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።

እንደ ሀገር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደ ተሻለ ምዕራፍም ለማሸጋገርም በፌደራል ደረጃ የተጀመረውን የመቶ ቀናት አቅድ ወደ ክልሉ በማመጣት የሚሰራበት አቅጣጫ መቀመጡን የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በተጨማሪ በተያዘው አዲስ ዓመት በተለይም በስራ እድል ፈጠራ የተጀመሩት ስራዎችን በማጠናከር ወጣቱን በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን አስረድተዋል።