በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል

585

መስከረም 9/2012 መንግስት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመደቡ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲዎችን ሕግ አክብረው ለመንቀሳቀስ የኃላፊነት ቅጽ መፈረም እንደሚጠበቅባቸውም ተገልጿል።

ነባር የከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት ተማሪዎች ምዝገባ ከመስከረም 5 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንዲሁም የአዳዲስ ተማሪዎች ቅበላ ከመስከረም 25 እስከ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንደሚካሔድ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ዛሬ በሰጡት መግለጫ በዚህ ዓመት 142 ሺህ 943 ተማሪዎች በመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይደለደላሉ።

ተማሪዎቹ ወደ ተቋማቱ ከመሔዳቸው በፊት በየወረዳቸው ስልጠና ከወሰዱ በኋላ  በቆይታቸው የግልና የጋራ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችል ቅጽ እንዲፈርሙ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ተማሪዎች በየተቋማቱ ለምዝገባ ሲቀርቡ ቤተሰቦቻቸው፣ ተማሪዎቹና የየወረዳቸው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ማረጋገጫ ማህተም ያረፈበት የኃላፊነት መውሰጃ ቅጽ ይዘው መቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሌላውን ኃይማኖት፣ ፖለቲካዊ እሳቤና ብሔር የሚያጣጥልና የሚያጎድፍ ጽሑፍና ምልክት ያለባቸውን አልባሳት መልበስ ወይም ቁሳቁሶችን መጠቀም እንደማይፈቀድ ገልጸው፤ ድርጊቱ ተፈጽሞ ሲገኝ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አስገንዝበዋል።

በማንኛውም ሁኔታ ተማሪዎች የዲስፕሊን ጥፋት ላይ ተሳትፈው በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ጉዳት ቢያደርሱና ለጥፋቱ ተባባሪ ሆነው ከተገኙ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የንብረቱን የዋጋ ግምት እንዲከፍሉ እንደሚደረግ አሳስበዋል።

በዚሁ የመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ መምህራን አገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎችን የመቅረጽ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመረዳት  ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ በአለባበስና በስነ-ምግባር አርአያ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የአስተዳደር ሰራተኞት፣ የተማሪ ወላጆች ወይም  አሳዲጊዎችና የአካባቢው ማሕበረሰብና አስተዳደር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በመንግስትና በግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ነው የተጠቆመው።